የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ በማልማት ገበያ ተኮር የንብ ማነብ ዘዴ እና የኅብረት ሥራ አመራር: የስልጠና መመሪያ ድንቁ ነጋሽ1, ጌታቸዉ ጎበና1, እዩኤል ግርማ3, ቃልኪዳን አየለ3, ዮዲት ባልቻ3, ረጋሳ በቀለ3, ኬኔት ዋሉሴ3 1 SOS Sahel Ethiopia 2 ሲዳማ ክልል የህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ 3 Alliance Bioversity International and CIAT December 2024 (ታህሳስ 2017 E.C) CGIAR Initiative on Diversification in East and Southern Africa Training Manual የጎልጃሞ መልሶ ያገገመ መሬት ምስል፤ በኬ-ላሊማ ቀበሌ ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ሲዳማ ክልል (የፎቶ ምስጋና፡ ለእዩኤል ግርማይ፤ 2017 ዓ.ም) ii መግቢያ ይህ ማኑዋል በ Alliance of Bioversity International and CIAT (ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም) እና ኤስ.ኦ. ኤስ ሳህል ኢትዮጵያ (SOS Sahel Ethiopia) ትብብር በ2017 ዓ.ም የተዘጋጀ ነው። ስለ ማንዋሉ አስፈላጊነት ይህ የስልጠና ማንዋል በወረዳና ቀበሌ ደረጃ ያሉትን የግብርና߹ እንስሣት ሀብትና የህብረት ስራ ባለሙያዎች እና የመሬት መልሶ ማልማት ፕሮግራም በሚተገበርበት አካባቢ (በኬ-ላሊማ ቀበሌ) የሚገኙ በማህበር የተደራጁ ወጣቶችና ሴቶችን ለማሰልጠንና አቅማቸዉን (ዕዉቀትና የተግባር ክህሎት) ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ነዉ። ማኑዋሉ በንብ ማነብ ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ንብ ማነብ ጥቅም፣ የንብ ማነብ እንዴት መጀመር እንደሚቻል፣ ለንቦች ተስማሚ ቦታ መምረጥ፣ የንብ መኖ (ቀሰም) እፅዋት መምረጥና ማልማት፣ የኅብረ ንብ እንክብካቤ፣ የንብ ውጤቶችን ማምረትና ለገበያ ማቀረብ፣ ከንብ ማነብ ገቢን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል፣ ህብረ ንቦችን እንዴት ክጠላት፣ ከበሸታና ከኬሚካል እንዴት መከላከል እንደሚቻል፣ በህብረት ስራ ተድራጅቶ መስራት የሚያስገኘዉን ጥቅም ለማሳወቅና በተግባር ላይ ለማዋል ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ማንዋሉን እንዴት መጠቀም ይቻላል የማንዋሉን ይዘት በሙሉ ወይም በከፊል እንደሰልጣኞች ደረጃ በሚያመች መልኩ መጠቀም ይቻላል። ማንዋሉ በሁሉም የመሬት መልሶ ማልማት ፕሮግራም በሚተገበርባቸዉ አካባቢዎች የሚገኙ ባለሞያዎች߹ ወጣቶችና ሴቶች እና ሌሎች አርሶ አደሮች እንዲያገልግል ታስቦ በአማርኛ ተዘጋጅቷል። እንዳስፈላጊነቱ ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ሊተረጎም ይችላል። ይህ ማኑዋል የሚከተሉትን ተከታታይ የሆኑ ሰባት ዋና ዋና የንብ ማነብ ሥልጠና ክፍሎችን ይዟል። እነዚህም፡ - ምዕራፍ 1. የንብ እርባታ እና አሰራር ዘዴዎች ክ ፍ ል 1፡ መሰረታዊ የንብ እርባታ ክፍል 2፡ የንብ ዕርባታ ዝግጅት፣ ጣቢያ መረጣና ማቋቋም ክፍል 3፡ ህብረ ንቦችን ማዛወርና መንከባከብ ክፍል 4፡ የንቦች ሥነ-ህይወትና ኅብረ ንቦችን ማባዛት ክ ፍ ል 5፡ የንብ ውጤቶች ክፍል 6፡ መሠረታዊ የንብ ጤና ክፍል 7፡ የእቅድ ዝግጅትና መረጃ አያያዝ ናቸው። ምዕራፍ 2. የኅብረት ሥራ አደረጃጀት፣ አስተዳደር፣ አመራርና መርሆዎች ክ ፍ ል 1፡ የሕብረት ሥራ ማህበር ትርጉም እና አስፈላጊነት ክ ፍ ል 2፡ የኀብረት ሥራ ማህበር ዓላማዎችና መርሆዎች ክ ፍ ል 3፡ የሕብረት ሥራ ማህበራት እሴቶች ክ ፍ ል 4፡ የሕብረት ሥራ ማህበራት የገንዘብ ምንጮች ክ ፍ ል 5፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት ምዝገባ ክ ፍ ል 6፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት ግዴታና መብት ክ ፍ ል 7፡ የሕብረት ሥራ ማህበራት ኮሚቴዎች ሥልጣንና ተግባር ክ ፍ ል 8፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት የሂሳብ አያያዝና ገንዘብ አጠቃቀም እያንዳንዱ ክፍል በጥልቀት ተግባር ተኮር ለማድረግ ተሞክሯል። በተጨማሪም ሥልጠናው በተግባር በሚሰጥበት ጊዜ በፊልሞች፣ ፖስተሮች፣ ፎቶግራፎች በምስለ ድራማ (Simulation) እና በተግባር የሚታገዝ ነው። iii እነዚህን የሥልጠና ክፍሎች በተናጠልም ሆነ በተከታታይ በሚሰጡበት ወቅት የሚከተሉትን ነጥቦች በመዳሰስና በዉይይት ወቅት በማካተት አሳታፊና አካታች የንብ ማነብ እና የኀብረት ሥራ ማህበር ሥርዓት ሂደት ማረጋጋጥ ይቻላል። • ለስልጠናዉ በሚደረገዉ ዝግጅት ወቅት አስቀድሞ ስልጠናዉ የሚካሄድበት ማህበረሰብ ዉስጥ ያለዉን ከንብ ማነብ ጋር የተያያዙ ፆታዊ መሠረት ያላቸዉ (gender roles and divisions) የሥራ ክፍፍሎችን መረዳት ያስፈልጋል። • ከዚህም ጋር ተያይዞ የማህበረሰቡን ባህልና ወግ በመረዳት የሥልጠናዉን ፕሮግራም ማዘጋጀትና ሥልጠናዉን ማካሄድ ያስፈልጋል። • የሥልጠናዉ ፕሮግራም በሚዘጋጅበት ወቅት የወጣት ሴቶችንና ወንዶችን፣ የአካል ጉዳት ያለባቸውን እንዲሁምየበለጠ ተጋላጨ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለመረዳት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ በሥልጠናዉ ይዘት ዉስጥ መካተታቸዉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ የቅድመ- ሥልጠና ፍላጎታቸዉን ያማከለ መሆኑን በማረጋገጥ የወጣቶችን ንቁ ተሳትፎ ማረገገጥ ያስፈልጋል። ይህንንም ለማድረግ የቅድመ-ሥልጠና መጠይቆችን መጠቀም (pre-test) ይቻላል። • የስልጠናዉ ቦታና ሰዓት የወጣት ሴቶችንና ወንዶችን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበና ፍላጎታቸዉን ያማከለ መሆኑን በማረጋገጥ የወጣቶችን ንቁ ተሳትፎ መረጋገጥ ይቻላል። • በሥልጠናዉ ላይ የምንጠቀመዉ ቋንቋ፣ አባባሎችና ምሳሌዎች ሁሉም ተሳታፊዎች ማለትም ወጣት ሴቶችና ወንዶች እንዲሁም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያማከሉና በይዘታቸዉም ክበረ-ነክ አለመሆናቸዉን ማረጋጋጥ ይገባል። • በሥልጠናዉ ላይ የምንጠቀማቸዉ ፊልሞች፣ ፖስተሮችና ፎቶግራፎች ዉጤታማ ንብ አናቢ ሴቶችንና ወንዶችን ያካተተ ማድረግ ይገባል። • አሰልጣኞች በሥልጠናዉ ሂደት ወቅት ወጣት ሴቶችና ወንዶች በነፃነት ሀሳባቸዉን የሚገልፁበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል። በዚህም መሠረት በተለይም ወጣት ሴቶችን ሆን ብሎ ሀሳብ እንዲሰጡ ማበረታታትና ማሳተፍ ይጠበቅባዋል። 4 ምዕራፍ 1፡ የንብ እርባታ እና አሰራር ዘዴዎች ክፍል 1፡ የንብ ማነብ አሰራር 1.1. የንብ ማነብ ጠቀሜታዎች ንቦች በህብረት የሚኖሩና ከዕፅዋት አበቦች ምግባቸውን ሰብስበው የሚመገቡ በራሪ ነፍሳት ናቸው። ንቦች በተፈጥሮ ሃብት ላይ ጥገኛ ከመሆናቸው የተነሳ በጫካ፣ በዋሻዎች፣ ለሌሎች እንስሳት ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች መኖሪያቸውን በመስራት፣ ጥሩ የቀሰም ዕፅዋት ስብጥር በሚገኝበት አካባቢ ምግባቸውን ከአበባዎች በማዘጋጀት የሚኖሩ ትንንሽ ፍጥረታት ናቸው። የሰው ልጅም ከዘመናት በፊት ለራሱ እንዲመቸው፣ እንዲቀርበውና እንዲጠቀምባቸው ሲል ንቦችን መቆጣጠርና ማርባት ጀመረ። ስለሆነም ንብ እርባታ ማለት የንብ ውጤቶችን ለሰው ልጅ ጥቅም እንዲውል የማድረግ ጥበብና ሳይንስ ነው። ንብ ማነብ ስራ ከሌሎች የግብርና ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር እጅግ በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ጠቃሜታዎች የሚሰጥና በማንኛውም መስፈርት አሉታዊ ተጽዕኖ የሌለው ሥራ ነው። የንብ ማነብ ዋናዋና ጥቅሞች • ንቦች ሰብሎችንና እፅዋቶችን በማዳቅል ምርትን በጥራትና በብዛት እንዲጨምር ያደርጋሉ፣ • ንቦች ማርና ሰምን እንዲሁም ድኝ (ፖለን)፣ ሙጫ (ፕሮፖሊስ)፣ የንብ ወተትና (ሮያል ጀሊ)፣ የንብ መርዝ (ቢ ቬነም) ያመርታሉ፣ • ንብ ማነብ በአነሰተኛ ወጭ ከፍተኛ ገቢ ሊያሰገኝ የሚችል የግብርና ሥራ ነው፣ • ንብ ማነብ ብዙ ጉልበት ስለማይጠይቅ በትርፍ ሰዓት የዕድሜ ክልልና ፆታን ሳይለይ 5 በማንኛውም የቤተሰብ አባላት በቀላሎ ሊካሄድ የሚችል ሥራ ነው፣ • ንቦች ሰውም ሆነ ሌሎች የቤት እንሰሳት የማይጠቀሙበትን የአበባ ወለላ (ኔክታር) እና ጽጌ ብናኝ (ፖለን) ስለሚጠቀሙ የምግብም ሆነ የመኖ ሽሚያ አያስከትሉም፣ • ንብ ማነብ እንደሌሎች የእርባታ ስራዎች የእለት ከእለት ክትትል አይጠይቅም፣ • ንቦች አካባቢን እና ስርዓተ ምህዳርን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፆኦ አላቸው፣ ለማር ምርት ሲባል ዕፅዋት ስለሚጠበቁ የአካባቢ ተፈጥሮ ሚዛን አይዛባም፣ • የንብ ማነብ ለብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሥራ እድልን ይፈጥራል። • የንብ ማነብ ስራ የመሬት ሽሚያን አያስከትልም፣ ሥራው ለሰብል ልማት ወይም ለእንስሳት እርባታ አመቺ ባልሆኑ ቦታዎች የሚካሄድ ከመሆኑም ሌላ የእርሻ መሬት በሌላቸው ግለሰቦች ጭምር ሊከናወን የሚችል የግብርና ሥራ ነው፣ • የንብ ማነብ በትንሽ መሬት ሊካሄድ ይችላል፣ በተከለሉና ባገገሙ ተራራማና ኮረብታማ ቦታዎች ላይ ኅብረ ንቦች ሊራቡና ማር ሊያመርቱ ይችላሉ፣ • ማር ለምግብነትና ለመድኃኒት አገልግሎት ይውላል፤ ማር፣ ሰም እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ምርቶች ተሸጠው ከፍተኛ የሆነ ገቢን ያስገኛሉ፣ • የንብ እርባታ ከሌሎች የግብርና ተግባራት ጋር በተጓዳኝ በተደጋጋፊነት ሊከናወን ይችላል፣ • ወጣቶች፣ ሌሎች ግለሰቦች ወይም ባለሀብቶች በተናጠልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው ልማቱን ሊያካሂዱት ይችላሉ። የንብ ማነብ አንጻራዊ ጠቀሜታ የንቦች አንፃራዊ ጠቀሜታዎች ማለትም ከሌሎች የስራ ዘርፎች በተለይም ሰብል ማምረት፣ እንስሳት እርባታ ከመሳሰሉ የግብርና ዘርፎች አንፃር ያለው ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ ከዚህ በታች ያሉትን ማየት እንችላለን። 1. ከማንኛውም የግብርና ሥራ ጋር የሃብት ውድድር አያደርግም 2. የተፈጥሮ ስነምህዳር ሚዛንን አያዛባም 3. በአነስተኛ መሬት ሊከናወን ይችላል 4. ለምርት መሬት ማስፋፋት (intensification) አገልግሎት ይጠቅማል 5. የመነሻና መንቀሳቀሻ ካፒታል አነስተኛና አደጋውም ዝቅተኛ ነው 6. የዕለት ተዕለት ክትትል አያሻውም (በትርፍ ጊዜ ወይም በተደረቢ ሥራነት ሊከናወን ይችላል) 7. ፆታና ዕድሜን ሳይለይ ሊሰራ ይችላል 8. ንቦች ባይኖሩ ሊባክኑ የሚችሉ ሃብቶችን ለመጠቀም ያስችለናል (ማር፣ ሰም፣ የንብ ሙጫ፣ የንብ ወተት፣ ድኝ፣ ማዳቀል ወዘተ) 9. አብዛኛዎቹ የንብ ውጤቶች ቶሎ የማይበላሹ ናቸው 10. የንብ ውጤቶች ከፍተኛ ገቢ ስለሚያስገኙ እንደ ቤተሰብ ገቢ ምንጭና የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኛነት ያገለግላሉ 11. ከፍተኛ የምግብ ጠቀሜታ አላቸው (ኢነርጂና ፕሮቲን) 12. የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል (ላልተስተካከለ የዝናብ ስርጭት ጉዳት አነስተኛ ተጠቂነት) 13. የገቢ እና የውጭ ንግድ ዕቃ ዓይነት ለማስፋት ይጠቅማል 14. ንቦች በማዳቀል ተግባራቸው የግብርና ምርቶችን (ሰብሎችን) ምርት ለማሳደግ ይጠቅማሉ ማሳሰቢያ ማንኛውም ሰው ወደ ንብ ስራ ከመግባቱ በፊት በንብ ንድፋት ከፍተኛ ጉዳት የማያሰተናግድ (Alergic) አለመሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። 6 1.2. የንብ እርባታ በኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ለንብ እርባታ ስራ ያላት አመቺነት ሃገራችን ኢትዮጵያ ባላት ስነ-ምህዳርና ከታች በተዘረዘሩት የተለያዩ ምክንያቶች ለንብ እርባታ ስራ አመች ነች። ከነዚህም ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። • ለንብ እርባታ ስራና ለንቦች መኖሪያነት በጣም አመች የሆነ የአየር ንብረት ያላት መሆኑ • ከ 6000 - 7000 በላይ በተለያዩ ወቅቶች የሚያብቡና ለንብ እርባታ ስራ በሃብት ምንጭነት የሚያገለግሉ የእጽዋት ዝርያዎች ያሉ መሆኑ • በሃገራችን እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ (ከ2 ሚሊዮን በላይ) በንብ እርባታ የተሰማሩና የካበተ ልምድ ያላቸው አርሶ አደሮች መኖራቸውና በዘርፉ በመሳተፍ ላይ ያሉ እንዲሁም ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች መኖራቸው • መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱና በዚሁ ላይ ከመንግስትና ከአርሶ አደሩ ጋር ለመስራት የገቡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መበራከት • የንብ እርባታ ስራን ከተለያዩ ጉዳቶች ለመጠበቅና ለማስፋፋት የሚጠቅም አዋጅና ደንብ በመንግስት መፅደቁና ለዚሁ ማስፈፀሚያ የሚያገለግለው መመሪያ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁ። የኢትዮጵያ ንብ ሃብት ልማት ተግዳሮቶች • ኋላ ቀር የአረባብ ዘዴ መከተላችን • በምርታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ህብረ-ንቦችን መጠቀማችን እና አለማስወገድ • በአሁኑ ሰዓት ያለው የህብረ-ንብ እጥረት • የንብ ማንቢያ መሳሪያዎች እጥረትና የጥራት ጉድለት • በእጃችን የሚገኙትን የተሻሻሉ ቴክኖሎጅዎችን በአግባቡ ወደ አርቢው አለማድረስና የደረሱትንም አፈፃፀም አለመከታተል • የደኖች በከፍተኛ ደረጃ መመናመንና የደን መልሶ ልማት ስራዎች በሚከናወነው ደረጃ ውጤታማ አለመሆን • የዘርፈ ብዙ ዕፀዋቶችን ለብቻ ለይቶ እንክብካቤ፣ ተከላና ልማት አለመኖር • የተለያዩ ኬሚካሎችን ለተለያዩ ዓላማዎች በሚል በዘልማድና አላግባብ መጠቀም • የተለያዩ የንብ ጠላቶችና በሽታ መኖር • አግባብነት ያለው ንቦችን የማዛወሪያ (የማሸጋገሪያ) ጊዜን አለመጠቀም • ንቦቹ በእያንዳንዱ የዓመቱ ወራት ውስጥ ምን ጊዜ ምን ያስፈልጋቸዋል በሚል የሚደረግ እንክብካቤ አለመኖር ወይንም አናሳ መሆን የኢትዮጵያ ንብ ሃብት ልማት እና የስራ እድል ፈጠራ በኢትዮጵያ የንብ ማነብ ስራ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እና ተሳትፎ ትልቅ አቅም አለው። የንብ ማነብ ወይም ንብ እርባታ ስራ ወጣቶችን የማብቃት እና ዘላቂ ልማት ለማምጣት ከፍተኛ አቅም አለው። ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በተለይም በገጠር እና በከተማ ዙሪያ ያሉ ልዩ አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ያቀርባል። የንብ ማነብ ስራ ለወጣቶች ስራ በመፍጠር፣ ኢኮኖሚ በማጎልበት፣ ክህሎት በማዳበር፣ አካባቢ ጥበቃን በማበረታታት፣ የወጣቶችን ማህበራዊ ተጽዕኖዎች በማሻሻል ለኢኮኖሚ ነፃነት እና ለማህበራዊ ልማት መንገድ ይሰጣል። ወጣት ኢትዮጵያውያን ተገቢውን ድጋፍና ግብአት ካገኙ ለወደፊት ብሩህ እና ዘላቂነት ያለውን የንብ እርባታ ሙሉ አቅም መጠቀም ይችላሉ። 7 1.3. የንብ እርባታ ዓይነቶችና አጠቃቀም ሀ) በባህላዊ ዘዴ ንብ ማነብና የባህላዊ ቀፎ አሠራር ይህ የማነብ ዘዴ አናቢው በልምድ ባካበተው እውቀት ከረጅም ዘመናት ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ስራ ነው። በአገራችን በብዛት የንብ ማነብ የሚካሄደው በአብዛኛው በባህላዊ ዘዴ ነው። ባህላዊ ንብ ቀፎዎች በቅርፃቸው፣ በይዘታቸውና በመጠናቸው ከቦታ ቦታ የሚለያዩ ሲሆኑ የሚሰሩበትም ቁሳቁሶች እንደየ አካባቢው ይለያያል። ለንብ ማነብ የሚያገለግሉት ባህላዊ ቀፎዎች የሚሰሩት በአካባቢ ከሚገኙ ቁሳቁስ ለምሳሌ ከሸምበቆ፣ ቀርከሃ፣ ሃረግና አጣናዎች፣ ግንድ ከቅርፊት፣ እበት፣ አመድና ጭቃ ከመሳሰሉት ቁሳቁሶች ነው። እነዚህ ለባህላዊ ቀፎ መስሪያነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ለረጅም ዓመታት ንብ አናቢው ኅብረተሰብ ሲገለገልባቸው የቆዩ ናቸው። ምስል 1፡ ባህላዊ የቀፎ ዓይነቶች ነባር ንብ አናቢዎች በንብ ቀፎ ማስቀመጫ ጋጣቸው ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ኅብረ-ንብ የያዙ ቅሎች ይታያሉ። እነዚህም ቅሎች የሚያገለግሉት ለህብረ-ንብ ማባዣነት ወይም ለማጥመጃነት ነው። በዚህ አኳኋን የተዘጋጁ የቅል ቀፎዎችን በመጠቀም በአንድ ወቅት እስክ 4 ኅብረ-ንብ ተከፍለው በመውጣት የኅብረ- ንባቸውን መጠን ያሳድጋሉ። ይህም አሰራር ዘዴ ደካማ ጎን ቢኖርበትም ንብ አናቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር መሆኑና በባለሙያተኞችም የሚደገፍ ልምድ መሆኑ ስራው እንዲቀጥል ይበረታታል። በአጠቃላይ የባህላዊ የንብ ቀፎ ዋና መገለጫው፡- • እንደየ አካባቢው የሚለያይ ቢሆንም በአማካኝ የቀፎው አማካይ ርዝመቱ አንድ ሜትር ሲሆን አፈጋኑ ሰፋ ያለ በዓይነ-ብልጡ በኩል ጠበብ ያለ ይሆናል፣ • ንቦች የማር እንጀራውን ከቀፎው የላይኛው ግድግዳ ጋር በማያያዝ ይሠሩታል፣ • በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አናቢዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙበት የቀፎ ቅርፅ ከአንድ ጫፍ በኩል ሰፊ ሆኖ በሌላው ጫፍ ደግሞ ጠበብ ተደርጎ የሚሠራ ሲሆን ማር የሚቆረጠው በአንድ በኩል ብቻ ሆኖ በተቃራኒው የንቦች መውጫና መግቢያ በኩል ማር ስለማይቆረጥበት ለብዙ ጊዜ የቆየ የማር እንጀራ ይኖራል፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አናቢዎች የሚሰሩት የቀፎ ዓይነት ደግሞ ስፋቱ በሁለቱም ጫፎች በኩል እኩል ሲሆን በሁለቱም ጫፍ በኩል ማር መቁረጥ ያስችላል፣ 8 • አልፎ አልፎ ደግሞ በሁለቱም ጫፍ ሰፋ ብሎ ከወገቡ ጠበብ ያለ ቅርፅ ያላቸው ቀፎዎችን የሚጠቀሙ አናቢዎች አሉ፣ • በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ አናቢዎች ደግሞ ከእበት፣ አመድና ጭቃ የሚሠራ ተገጣጣሚ ቀፎ ይጠቀማሉ፣ ይህ ተገጣጣሚ ቀፎ ለማር ቆረጣና ንቦችን ለመክፈል አመች ነው። ባህላዊ ቀፎ የሚጠቀሙ አናቢዎች አብዛኛውን ጊዜ ብዛት ያለው ቀፎዎች ስላሏቸው የተወሰኑት ብቻ በኅብረ ንቦች የተሞሉ ናቸው። ይህ በስፋት በባህላዊ ቀፎ የሚካሄድ የማነብ ዘዴ ከአውሮፓ ንቦች ይልቅ ለአፍሪካ ንቦች ተስማሚ ነው። ምክንያቱም የአፍሪካ ንቦች ያሉበት ቀፎ ካልተመቻቸውና በአካባቢው የንቦች ቀሰም እጥረት ሲደርስ የመሰደድና ቀፏቸውን ለቀው የመሄድ ባህርይ ስላላቸው ነው። ከማር ቆረጣ በኋላ ንቡ ቢሰደድ ሌላ የተሰደደ ወይም የተዋለደ ንብ እስከሚገባበት ድረስ ቀፎው ባዶውን ይቀመጣል። የባህላዊ ቀፎዎች ከአካባቢው ቁሳቁስ በአናቢዎች ስለሚሰሩና በግዥም ርካሽ ስለሆኑ አናቢዎች ብዙ ቀፎዎችን በመሥራት ወይም በመግዛት የንብ ማነብ ሥራውን በቀላሉ ሊያስፋፉት ይችላሉ። በባህላዊ ዘዴ ንብ ማነብ በሁለት ዋና ክፍሎች ሊከፈል ይችላል። አንደኛዉ ባህላዊ ቀፎዎችን በጫካ ዉስጥ በዛፎች ላይ በማስቀመጥ የሚከናወን ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ቀፎዎችን በተሰራላቸዉ ጋጣ ዉስጥ በማስቀመጥ ወይም በቤት ዙሪያ በመደርደር የሚከናወን የንብ ማነብ ዘዴ ነዉ። የመጀመሪያዉ በጫካ ዉስጥ የንብ ቀፎዎችን (Forest beekeeping) በማስቀመጥ ንብ የማነብ ዘዴ ለንቦች ቀሰም እፅዋቶች በብዛት ከመገኘታቸዉ አንጻር፣ አከባቢ ጥበቃና ከመንደር ራቅ በማለታቸዉ የተነሳ በሰዎችና በእንሰሳት ላይ አደጋ ስለማያደርሱ ጠቀሜታ አላቸዉ በተቃራኒዉ ደግሞ ይህ ዘዴ በማር ቆረጣ ወቅት በንቦችና በማር ቆራጩ/ጯ ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊደርስ ይችላል። እንዲሁም ይህ የንብ ማነብ ሥርዓት ከመኖሪያ አካባቢ ራቅ ባሉ ጫካዎችና ረጃጅም ዛፎች ላይ ከመከናወኑ የተነሳ ለሴቶች ተሳትፎ አመቺ አይደለም። ሁለተኛዉ የንብ ቀፎዎችን በቤት ዙሪያ በመደርደር ወይም በተሰራላቸዉ ጋጣ ዉስጥ በማስቀመጥ የሚከናወነዉ የንብ ማነብ ዘዴ (backyard beekeeping) ከቤት አቅራቢያ የሚከናወን በመሆኑ ለሴቶችና ለተለያዩ የቤተሰብ ክፍሎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ምቹ ነዉ። ሴቶች በቀላሉ የንብ ማነቡን ሥራ ከሌሎች ኃላፊነቶቻቸዉ ጋር ለማጣመር የተሻለ እድል ያገኛሉ። ይህ ዘዴ ረጃጅም ጎዞዎችን መድረግ ስለማይጠይቅ በግልም ሆነ በቡድን ለመስራት ለሴቶች ተመራጭ ነዉ። የባህላዊ ቀፎ አሠራርን ማሻሻል የባህላዊ ቀፎ አሠራር ለመማር የአካባቢ አናቢዎችን በእጅጉ ማማከር ያስፈልጋል። በባህላዊ ቀፎ የማነብ ዘዴዎች የማይለወጡ ሳይሆኑ በጊዜያት ብዛት በአናቢዎች ፍላጎት መሠረት እየተሻሻሉ የመጡ ናቸው (ከላይ በምስል 1 ይመልከቱ)። ባህላዊ ቀፎ ምርትን ለማሳደግ ከሚያስችሉ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ቀፎውን ሰፋ አድርጎ መሥራት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሁለቱም በኩል ማምረት እንዲቻል አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል። 9 ምስል 2፡ የተሻሻለው ባህላዊ ቀፎ ዲዛይን፤ እርዝመቱ 90 ሳ.ሜ የውስጥ ለውስጥ ስፋቱ 40ሳ.ሜ. ይህን የቀፎ አሰራር በመጠቀም ማሩን በሁለቱም በኩል በማፈራረቅ ማምረት ስለሚያስችል አንዴ የተሰራው የማር እንጀራ ብዙ ጊዜ ቀፎው ውስጥ ስለማይቆይ ለህብረ-ንቡ የተሻለ ጤንነት ከመስጠቱም በተጨማሪ ለእናት ንብም እንቁላሏን ለመጣል አመች ሁኔታን ይፈጥርላታል። የባህላዊ ቀፎ ጥሩ መገለጫ ባህሪያት ንቦችን ማገናዘብ • ንቦች ላይ ጉዳት ሳይደርስ በሁለቱም ጫፍ በኩል ማር ማምረት የሚያስችል • ትክክለኛ መጠን ያለው - ለንቦች መራቢያ/መባዣና ለማር ምርት በቂ ስፋት ያለው • ንቦችን ከጠላቶቻቸው መከላከል የሚያስችል - ለንቦች ተስማሚ መውጫና መግቢያ ቀዳዳ (ዓይነ ብልጥ) ያለው • ንቦችን በቀላሉ ሊያናፍስ ከሚችል ቁሳቁስ የተሠራ አካባቢን ማገናዘብ • አካባቢን ከማይጎዱ ወይም ከማይበክሉ ቁሳቁሶች የተሠራ - ዛፎችን የምንጠቀም ከሆነ • ሌሎች ዛፎችን መንከባከብና መትከል ያስፈልጋል የማነብ ዘዴውን ማገናዘብ • ጥሩ ዲዛይን ያላቸው - አናቢዎች እጩን ሳይጎዱ ማር መቁረጥ የሚያስችል በር ወይም ቀዳዳ ያለው • ለብዙ ጊዜ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ያስታውሱ! ባህላዊ ቀፎዎች ለብዙ ዘመናት ጥቅም ላይ የዋሉና ለንቦች ተስማሚ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ሲሆኑ በአግባቡ ከተያዙ በጣም ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ። ባህላዊ ቀፎዎችን ሙሉ በሙሉ በሌላ የቀፎ ዓይነቶች መተካት አስፈላጊ አይደለም። በአፍሪካየአዋጭነት ስሌት ሲሠራ ባህላዊ ቀፎዎች ከሌሎች የቀፎ ዓይነቶች ጋር ሲነጻጸሩ የተሻሉ ናቸው። 10 ሐ) በርብራብ ቀፎ የማነብ ዘዴ የርብራብ ቀፎ አሰራር የርብራብ ቀፎ የቀፎ ዓይነት የኬንያ ቶፕ ባር ቀፎ፣ የጨፈቃ ቀፎ፤ ኢትዮ-ርብራብ ቀፎ እና የሽግግር ቀፎ በመባል የሚጠራ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚታወቀው የሽግግር ቀፎ በመባል ነው። በዚህ የስልጠና ማኑዋል ውስጥ የርብራብ ቀፎ እየተባለ ይጠራል። ይህን ቀፎ በተለያዩ አገሮች በጣውላ በመስራት ቢታወቅም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ከጣውላ መስራቱ ለበለጠ ደን መጨፍጨፍ ምክንያት ስለሚሆን አጠቃላይ የቀፎውን ይዘት በመጠበቅ ከተለያዩና በአካባቢ በቀላሉ ከሚገኙ ቁሳቁሶች ማለትም ከሸንበቆ፣ ከቀርከሃ፣ ከጭቃ፣ ከእበትና አመድና ከአጣናዎች እየተሠራ ጥቅም በመስጠት ላይ ይገኛል (ምስል 3 ይመልከቱ)። ምስል 3፡ የርብራብ ቀፎ (ግራ - ከእበትና አመድ የተሰራ፤ ቀኝ - ከእንጨት ሸምበቆና እበት የተለቀለቀ) በምስል፡ 3 እንደሚታየው የርብራብ ቀፎ ከታች ጠበብ ብሎ ከላይ ሰፋ ያለ ሳጥን መሰል ቅርጽ ያለው ሲሆን ከላይኛው ጠርዝ ርብራቦች ይደረደሩበታል። ንቦችም የማር እንጀራውን የሚሠሩት ከርብራቦች የውስጠኛው ክፍል ላይ ነው። ስለዚህ አናቢዎች እያንዳንዱን ርብራብ በቀላሉ በማንሳት መመልከት ስለሚያስችል ያልበሰለ ማርና እጭ የያዘውን ርብራብ በመለየት የበሰለውን ማር ብቻ መቁረጥ ይችላሉ። በዚህ ቀፎ የውስጥ ቁጥጥር ማድረግ ስለሚቻል ንቦች በውስጣቸው ሊፈጠር የሚችለውን ችግር በቀላሉ ማወቅ ስለሚቻል አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይቻላል። በአካባቢ ቁሳቁስ የርብራብ ቀፎ አሠራር ከሸምበቆ ወይም ከሌሎች የእንጨት ዉጤቶች የርብራብ ቀፎን በሚከተለው መንገድ መሥራት ይቻላል። • ሸምበቆው በመጀመሪያ ለሁለት ይሠነጠቃል፣ • ሁለቱ ተቃራኒ ግድግዳዎች አንድ አይነት 30 ሴንቲ ሜትር ስፋትና 100 ሴንቲ ሜትር ርዝመት እንዲኖራቸው ሆነው ይሠራሉ፣ • ቀፎው የእበት ቅብ እንዲይዝ ሸምበቆዎቹ የውጭና የውስጥ አካላቸው ተሰባጥሮ መሰራት አለበት፣ • የቀፎው ወለል ደግሞ 24 ሴንቲ ሜትር ስፋት ሲኖረው እርዝመቱ ግን ለንቦች ማረፊያና ማኮብኮቢያ ያስታውሱ! በርብራብ ቀፎ የማነብ ዘዴ ለጀማሪም ሆነ የባህላዊ ቀፎ ለሚጠቀሙ አናቢዎች ተስማሚ ነው። በባህላዊ ቀፎ ንብ የሚያንቡ ግለሰቦች የርብራብ ቀፎን መጠቀም የሚሰጠውን ጥቅም ማወቅ ይኖርባቸዋል። የርብራብ ቀፎን በመጠቀም በቀላል ወጪ የንብ ማናባት ስራን ማስፋፋት ያስችላል፣ ገቢንም ያሳድጋል። 11 በአምስት ሴንቲ ሜትር እንዲበልጥ ሆኖ በ105 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ይሠራል፣ • ሁለቱ ግድግዳዎች ከወለሉ ጋር ሲገጣጠሙ ሙሉ በሙሉ ከታችኛው ወለል ላይ እንዲያርፉ ይደረግና ከወለሉ የተረፈችው 5 ሳ.ሜ ለንቦች ማኮብኮቢያ በመሆን ታገለግላለች፣ • ቀፎው ሲገጣጠም በአፉ አካባቢ ሰፋ ብሎ ወደታች እየጠበበ ይሄዳል፣ • በሁለቱ ግድግዳዎች መገናኛ ላይ ከ950 - 1180 (በአማካኝ 1100) አንግል ይመጣል፣ • ቀፎው ከተሠራ በኋላ በእበትና በአመድ እያሹ በውጭም በውስጥም መቀባትና መለቅለቅ አለባቸው። የቀፎው መጠን እንደ አካባቢው ሁኔታ ሊለያይ ይችላል፤ አካባቢው ጥሩ የቀሰም እጽዋት በብዛት የሚገኙበትና ጠንካራ ኅብረ ንብ ካለ ቀፎውን ማስረዘም ይቻላል። በተቃራኒው ደካማ ኅብረ ንብና አካባቢው በቂ የቀሠም እጽዋት የሌለው ከሆነ መጠኑን ማሳነስ ይቻላል። ይህን ለማረጋገጥ በአካባቢው የሚገኙ ንቦች ለቀው የሄዱበትን ባህላዊ ቀፎ ውስጥ የተሠራውን የእንጀራ ብዛት በመቁጠርና እርዝመቱን በመለካት የእርብራብ ቀፎውን ርዝመትና ስፋት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። 12 ምስል 4: የርብራብ ቀፎ አሰራር ዲዛይን ከከብት እበትና ከአመድ ጋር በማቀላቀል የሚሠራ ቀፎ በቅርጹ ይለያይ እንጂ ይህ አሠራር እናቶች ባህላዊ ቀፎን ከእበትና ከአመድ ጋር በመቀላቀል እንደሚሠሩት አይነት ነው።  ሁለት እጅ እበትና አንድ እጅ አመድ በማድረግ ውኃ እየጨመሩ ማቡካት፣  በደንብ እንዲብለላ ማድረግ፣  ከመሠረቱ ጀምሮ ቀስ በቀስ እየጠነከረ እንዲሄድ ከደረቀ በኋላ መቀጠል፣  የቀፎውን ክፍተት በቶፕ ባር ልክ አስተካክሎ መጨረስ፣  አይነብልጥና ማጨሻ ቀዳዳዎችን ማዘጋጀት።  የማር እንጀራ መገንቢያ ውስጠኛ አካል ርዝመት 42 ሳ.ሜ ይሆናል። ርብራብ ቀፎ በሚሰራበት ጊዜ የሚከተሉተን ነጥቦች መገንዘብ ጠቃሚ ነው  ርብራብ በሚሠራበት ጊዜ ከቀፎው በበለጠ ጥንቃቄና ትክክለኛ የሆነ ልኬትን ይፈልጋል፣  እስከ አሁን በተገኘው ልምድና ተሞክሮ መሠረት ከተለያዩ እንጨቶች መስራት የሚቻል ቢሆንም ተመራጩ ግን የሚሠራበት እንጨት ቅርጽና መጠኑን የማይቀይር መሆን ይኖርበታል፣  ለእኛ አገር ኅብረ ንቦች የርብራቡ ስፋት በትክክል 3.2 ሴንቲ ሜትር (ንቦች በአማካኝ 2.5 ሴ.ሜ ስፋት ያለው የማር እንጀራ ይሠራሉ፤ ቀሪው 0.7 ሴ.ሜ የንቦች መንቀሳቀሻ ቦታ ነው) ሆኖ ርዝመቱ ደግሞ እስከ 52 ሳ.ሜ ሊሆን ይችላል። ምስል 5፡ ከሸንበቆ የተሠሩ የርብራብ ቀፎዎች በተዘጋጀላቸው ጋጣ ውስጥ በርብራብ ቀፎ አሰራር ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ርብራቡ በሚጠረብበት ጊዜ ከትክክለኛው ስፋት ውጭ ከተሠራ ሁለት ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። 1. በሚጠብበት ጊዜ (ከ3.2 ሴ.ሜ ሲያንስ)፡ ንቦች የማር እንጀራን በአንድ ቶፕ ባር ላይ ለመስራት ስፋቱ ስለሚጠባቸው ከአንድ ቶፕ ባር በላይ ሊጠቀሙ ይችላሉ፤ ስለሆነም በቆረጣ፣ በቁጥጥርም ሆነ በሌሎች ሥራዎች ጊዜ አንዱ ቶፕ ባር ሲነሳ እንጀራው ተቆርቶ በመውደቅ ንቦችን ይገድላል፤ ለስራም ምቹ አይደለም። 2. በሚሰፋበት ጊዜ (ከ3.2 ሴ.ሜ ሲበልጥ) ፡ በዚህ ጊዜ ንቦች በአንድ ርብራብ ላይ እንጀራ መስራት ጀምረው ትርፍ ቦታ ከዚያው ርብራብ ላይ ስለሚኖር ሌላ እንጀራ ከዚያው ርብራብ ላይ ይቀጥሉበታል፤ ስለማይበቃ ደግሞ ከሁለተኛው ርብራብ ጋር ያያይዙታል። ስለሆነም በሚጠብበት ጊዜ እንደተጠቀሰው በቆረጣ፣ በቁጥጥር ወይም በከፈላ ጊዜ ተመሳሳይ ችግር ሊያጋጥም ይችላል። ያስታውሱ! ርብራቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ስራ ስለሆን አናቢዎች ልይላውን የቀፎ ክፍል ከሰሩ በኋላ ርብራቡን በጣውላ ቤት ማስራት ይችላሉ። ርብራብ ቀፎን በብዛት መሥራት የሥራ እድልን የሚፈጥርና ተጨማሪ ገቢን የሚያስገኝ ተግባር ነው። 11 12 መ) በፍሬም ቀፎ ንብ ማነብ ይህ የማነብ ዘዴ ያደጉ አገሮች ካለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ጀምሮ ሲገለገሉበት የቆየ ቴክኖሎጂ ነው። የዚህ ቴክኖሎጂ አመጣጥ ከተሻሻሉ የማናቢያ መሳሪያዎች መፈልሰፍ ጋር የተቆራኘ ነው። ቴክኖሎጂው ወደ አገራችን የገባው እ.ኤ.አ. 1970 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ዘመናዊ ቀፎ፣ ባለፍሬም ቀፎ፣ የሳጥን ቀፎ፣ በመባል ይታወቃል። በዚህ ማኑዋል ውስጥ የፍሬም ቀፎ እየተባለ ይጠራል። በዚህ ቴክኖሎጂ መጠቀም ንቦች የሚጋግሩት የማር እንጀራ ተንቀሳቃሽ ፍሬም ላይ በመሆኑ የማር ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ በቀላሉ ኅብረ ንቡን የውስጥ ቁጥጥር ማካሄድና ሌሎች በርካታ ምርቶችንም ማምረት ያስችላል። እንደሁም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለውን ኅብረ ንብ ቁጥር በማስፋትና በማዘመን የበለጠ ተጠቃሚ መሆን ያስችላል። የፍሬም ቀፎ በዋነኛነት ከጣውላ የሚሠራ ባለ አራት ማዕዘን ሳጥን መሰል ሲሆን እስከ ሶስትና ከዚያም በላይ የሚሆን ተደራቢ ያለው ሆኖ በእያንዳንዱ ተደራቢ ውስጥ በአብዛኛው አስር አስር ባለ አራት ማዕዘን ተንቀሳቃሽ ፍሬሞች ይኖሩታል። ፍሬሞች የማር እንጀራውን መሸከም እንዲችሉ በማይዝግ የፍሬም ሽቦዎች ይወጠሩባቸዋል። በፍሬም ቀፎ ለማነብ የሚያስፈልጉ ወሳኝ መሳሪያዎች የሰም ማተሚያ፣ የማር ማጣርያ፣ የንግሥት ንብ ማገጃ፣ የፍሬም ሽቦ፣ የማር እንጀራ መግለጫ ሹካ፣ የተጋገረ የሰም እንጀራ ማያያዣ ናቸው። እነዚህም የማናቢያ መሳሪያዎች ውድና አብዛኛውን ጊዜ በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ መሳሪያዎችን ለመጠቀም ዕውቀት ስለሚያስፈልግ አናቢዎች በቂ ሥልጠና ሳያገኙ መሳሪያዎችን መጠቀም የለባቸውም። በአሁኑ ሰዓት የፍሬም ቀፎውን ዋጋ ለመቀነስ እንዲያስችል ከቀርቀሃ እና በሌሎች ቁሳቀሶች እየተሠራ በሙከራ ላይ ይገኛል። የፍሬም ቀፎን አገልግሎት ላይ ለማዋል በቂ ክህሎት የሚያስፈልገው ቢሆንም ከባህላዊና ከርብራብ ቀፎ ጋር ሲነጻጸር በጥራቱም ሆነ በመጠኑ የተሻለ የማር ምርት ያስገኛል። በተጨማሪም የተለያዩ የንብ ወጤቶችን ለማምረት አመቺ ነው። ሠ) የቀፎ ዓይነቶችን ማነጻጸር አናቢዎች አንድን የቀፎ ዓይነት ከመምረጣቸው በፊት ወይም ያላቸውን ቀፎ በሌላ ከመቀየራቸው በፊት ምን ማግኘት እንደሚፈልጉና ስለተለያዩ ቀፎዎች ጠንካራና ደካማ ጎኖች በግልጽ መረዳት ይኖርባቸዋል። የሦስቱም የቀፎ ዓይነቶች ጠንካራና ደካማ ጎኖች ቀጠሎ ባለው ሠንጠረዥ ቀርበዋል። 13 ሠንጠረዥ 1: በባህላዊ፡ ርብራብና ፍሬም ቀፎዎች የማናቢያ ዘዴ ጠንካራና ደካማ ጎን ባህላዊ ቀፎ ጠንካራ ጎን • ዋጋው አነስተኛ ነው • ከወጪው አንጻር አዋጪ ነው • የአካባቢ እውቀትንና ሃብትን ይጠቀማል • ለአፍሪካ የንብ ዝርያዎች ተስማሚ ነው • ሌቦችን አይስብም • ማርና ሰም ማምረት ያስችላል • ብዛት ካለው ቀፎ የተሻለ ማር ማግኘት ያስችላል • የንብ በሽታ በብዛት አያጠቃውም። ደካማ ጎን • ማር መድረሱን ለማወቅ አያስችልም • በማር ቆረጣ ወቅት ብዙ ንቦች ይሞታሉ • እጩ ሳይጎዳ ማሩን ለመቁረጥ አያስችልም • የተቆረጠውን እጭ፣ ድኝ፣ ያልበሰለ ማር መልሶ ቀፎ ውስጥ ለማስቀመጥ አያስችልም • አበዛኛውን ጊዜ አናቢው የመከላከያ ትጥቅ ስለማይጠቀም ንቦችን ለማሸሽ ብዙ ጭስ ስለሚጠቀም ማሩ የጭስ ጣዕም ሊኖረው ይችላል • በባህላዊ ቀፎ አነባብ ዘዴ ዛፍ ላይ መውጣትንና ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ የሴቶችን • ተሳትፎ ገድቦት ቆይቷል። የርብራብ ቀፎ ጠንካራ ጎን • እያንዳንዱን የማር እንጀራ በማንሳት የቀፎ ውስጥ ፍተሻ ማድረግ ያስችላል • የተሠራውን የማር መጠን ማወቅ ይቻላል • ንቦች ሳይረበሹ ማር መቁረጥ ይቻላል • እጩ ሳይጎዳ የበሰለውን ማር መቁረጥ ያስችላል • ማርና ሰም ማምረት ያስችላል • ለጀማሪ አናቢዎች ተስማሚ ነው • በርብራብ ቀፎ ንቦችን ማነብ ዘዴ ሴቶችን አሳታፊ ነው:: ደካማ ጎን • በአንፃራዊነት ዋጋው ውድ ነው • ተጨማሪ እውቀት ይጠይቃል • በሰም በል ትል በቀላሉ ይጠቃል • በየጊዜው ቀፎው ሲከፈት ንቦች ተረብሸው ሊሰደዱ ይችላሉ • ቀፎውን ለመክፈት የተሟላ ትጥቅ ያስፈልጋል። የፍሬም ቀፎ ጠንካራ ጎን • እያንዳንዱን የማር እንጀራ በማንሳት የቀፎ ውስጥ ፍተሻ ማድረግ ያስችላል • የተሠራውን የማር መጠን ማወቅ ይቻላል • ንቦች ሳይረበሹ ማር መቁረጥ ይቻላል • ንጹህ የተጣራ ማር ማምረት ያስችላል • ወለላው ማር ከተጣራ በኋላ ባዶውን የማር እንጀራ መልሶ ቀፎ ውስጥ በማስገባት በድጋሚ ማር ማምረት ይቻላል • በጉዞ ላይ የማር እንጀራው ስለማይሰበር በቀላሉ • ማጓጓዝ ይቻላል • በባለ ፍሬም ቀፎ ንቦችን ማነብ ዘዴ ሴቶችን አሳታፊ ነው። ደካማ ጎን • ዋጋው በአንጻራዊነት ውድ ነው • ተጨማሪ መገልገያ ቁሳቁሶች ያስፈልጉታል • ኅብረ-ንቡን ለመቆጣጠርም ሆነ ቀፎ ለመክፈት ሙሉ ትጥቅ ያስፈልገዋል • በቂ ዕውቀትና ክህሎት ይጠይቃል • በየጊዜው ቀፎው ሲከፈት ንቦች ተረብሸው ሊሰደዱ ይችለሉ። 14 ክፍል 2፡ የንብ እርባታ ዝግጅት፣ ጣቢያ መረጣና ማቋቋም 2.1. የንብ ማነብ ግብዓት ማሟላት የማነቢያ መሳሪያዎችና ቁሳቁስ የንብ ማነብ በቀላሉ የሚጀመር የግብርና ዘርፍ ነው። ሥራው በትንሽ ገንዘብ ሊጀመር ይችላል። የንብ ማነብን ለመጀመር የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ኅብረ ንብ፣ ቀፎ፣ የንብ ንድፋት መከላከያ ትጥቆች እና ሌሎች መሳሪያዎች (ማጨሻ፣ ብሩሽ፣ የእጅ ባትሪ፣ የማር መጭመቂያ ወይም ማጣሪያ፣ እንዳስፈላጊነቱ መሮ፣ የሰም ማተሚያ) የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ ቁሳቁሶች ገበያ ላይ በቀላሉ ይገኛሉ። ወደ ንብ እርባታ ስራው ከመግባታችን በፊት እነዚህን ግብዓቶች በአካባቢያችን መኖራቸውን ማረጋገጥ ወይም ሊገኙ የሚችሉበትን አማራጭ ማየት ያስፈልጋል። ቀፎው የአካባቢ ቁሳቁስ በመጠቀም በአናቢዎች ሊዘጋጅ ወይም ከአካባቢ ገበያ በቀላሉ ሊገዛ ይችላል። እንደ ማር ማጣሪያ፣ መጭመቂያ፣ ሰም ማተሚያ ያሉ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸውን የማነቢያና የማቀነባበሪያ ቁሳቁሶችን በጋራ (በማህበር) በመደራጀት መግዛትና መጠቀም ይቻላል። የንብ ንድፋት መከላከያ አልባሳት የንብ ንድፋት መከላከያ ትጥቆች (ጓንት፣ ዓይነ ርግብ፣ ቱታና ቦት ጫማ) ነቦች በአናቢው ላይ ጉዳት እናዳያደርሱ እና እነሱም እናዳይሞቱ ለመከላከል የሚያገለግል ሲሆን አልባሳቱን ባካባቢ ቁሳቁስ ማዘጋጀት ወይም በተመሳሳይ ቁሳቁስ መተካት ይቻላል። ነገር ግን አንድ አናቢ የንብ ንድፋት መከላከያ ትጥቆችን ሳይለብስ ወደ ንቦች መቅረብ የለበትም። ህብረ ንብ (የንብ መንጋ) ኅብረ ንቦችን በሚኖሩበት አካባቢ ቀፎ ዛፍ ላይ በመስቀል መያዝ ወይም በአካባቢው ከሚገኙ አናቢዎች በግዥ ማግኘት ይቻላል ወይም ከቤተሰብ በስጦታ ሊገኝ ይቻላል። የህብረ ንብ መንጋ የምናጠምድ ከሆነ ቀፎው ንቦች የሚወዱት ዕፅዋት ወይም ሰም መታጠን ይኖርበታል። ኅብረ ንቦችን ከጫካም ሆነ በግዥ ካገኘን በኋላ በቀጣይ ማድረግ የሚገባን ለንቦች ተስማሚ ወደ ሆነ ቦታ ማጓጓዝና ማስቀመጥ ነው። ኅብረ ንቦችን ስናጓጉዝ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱና ንቦችም እንዳይጎዱ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መሆን አለበት። ጠቃሚ ምክር • አንድ ግለሰብ አናቢ ለመሆን ከፈለገ በቅድሚያ ከንብ ንድፋት አለርጂ ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልገዋል። ይህ በጤና አገልግሎት መስጫ ተቋሞች ሊረጋገጥ ይችላል። • በተሻሻሉ የንብ ማናቢያ ቀፎዎች ተጠቃሚ ለመሆን የንቦች ንድፋት መከላከያ ትጥቆችን መጠቀም አስፈላጊነቱን መገንዘብ ያስፈልጋል። እነዚህ የማናቢያ ትጥቆች ከ3-5 ዓመት ሊያገለግሉ ስለሚችሉ ከስራ በኋላ በተገቢው ስፍራ ማስቀመጥዎን አይዘንጉ። 15 ምስል 6፡ የአናቢ ሙሉ ትጥቅ 2.2. የንብ ማናቢያ ቦታ መምረጥና የንብ ጋጣ መስራት የንብ ማናቢያ ቦታ መምረጥ የንብ እርባታ ጣቢያ (አፒያሪ) የንብ ቀፎዎች የሚቀመጡበት ቦታ ነው። ቃሉ እንዲሁ ንቦች የሚረቡበት እና ተዋልደው የሚወጡበትን ማንኛውንም ስፍራ ለማመልከት ያገለግላል። የንቦች የመቅሰም ባህርይ የፅጌ ብናኝና የፅጌ ወለላን ያሉበትን ቦታ የማወቅ ችሎታቸው ንቦችን በጣም ውጤታማ የፅጌ ብናኝና የፅጌ ወለላ ቀሳሚዎች ያደርጋቸዋል። ሌላው ውጤታማ ቀሳሚ ያደረጋቸው ባህርይ በአንድ ጉዞ አንድን የቀሰም ዓይነት ብቻ መቅሰም መቻላቸው ነው። • ይህ ችሎታቸው ንቦችን የተሻለ ቀሰም ወደሚገኝበት በቀላሉ እንዲሄዱና እንዲፈልጉ ያስችላቸዋል • ስለ ቀሰም ባህሪ መረጃ የሚከተሉትን ለመገመት ሊያገለግል ይችላል- o በንብ ቀፎዎች እና በንብ እፅዋት መካከል ያለው አነስተኛ ርቀት እንዲጠበቅ o የንብ ቀሰም ዕፅዋት ምርጫ ለማድረግ o ትክክለኛ ወቅታዊ አስተዳደር ለማድረግ 16 o ሁሉንም ሊሆኑ የሚችሉ ጥቅሞችን ለመውሰድ o ንቦች ያልተፈለገ ፅጌ ብናኝ እንዳይቀስሙ ለመከላከል o ያልተፈለጉ የአበባ ዱቄቶች ፍሰት ስጋትን ለመቀነስ በእርግጥ የመቅሰም ባህሪ የሚወሰነው የዓመቱ ወቅት፣ የህብረ-ንቡ ሁኔታ፣ የምግብ ምንጭ ስርጭት እንዲሁም በእያንዳንዳቸው ህብረ-ንቦች መካከል የእንቅስቃሴ ልዩነት ሊሆን ይችላል። የንብ እርባታ ጣቢያ ዓይነቶች የንብ እርባታ ጣቢያ ዓይነቶች እንደየተቋቋሙበት አላማቸው የሚከተሉትን ሊሆኑ ይችላሉ • የግል (Individuals apiary) • የልማት ፕሮጀክት (Development project apiary) • ሰርቶ ማሳያ (Demonstration apiary) • የምርምር ጣቢያ (Research site apiary) • የንግድ (Commercial apiary) የንብ ማናቢያ ቦታ ለመምረጥ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ንቦች ከሌሎች እንስሳት በተለየ መልኩ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ተስማሚ ቦታ መምረጥ ትልቅ ተግባር ነው። ኅብረ ንቦች በሚያመቻቸው ስፍራ በጫካ፣ በዱር በገደል፣ በዋሻ በመሳሰሉት የተፈጥሮ ቦታዎች ይኖራሉ። እነዚህን ኅብረ ንቦች በመያዝ ማነብ ይቻላል። በመጀመሪያ ህብረ-ንቦችን ለስራቸው አመች በሆነ ቀፎ ውስጥና በሚስማማቸው አካባቢ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ከመስክ በተግባር እንደሚታየው ኅብረ ንቦችን በመኖሪያ ቤት ውስጥም ሆነ በጓሮ አካባቢ፣ በተከለሉ ደኖች፣ በጫካ አስቀምጦ ማነብ የተለመደ ተግባር ነው። በአጠቃላይ የንብ ማነብን ለመጀመርና ውጤታማ ለመሆን ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ተስማሚ ሥፍራ መምረጥ ሲሆን የማናቢያ ቦታው የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል። 1. የቀሰም እፅዋት በአካባቢው በብዛት የቀሰም እፅዋት የሚገኙበት፤ የማናቢያ ስፍራው ቢቻል የተለያዩ የቀሰም እፅዋት በበቂ መጠን በሚገኝበት አካባቢ እና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት፣ የጥራጥሬና የቅመማ ቅመም ሰብሎችን ማዳቀል በሚቻልበት አካባቢ ቢሆን ይመረጣል፣ ጠቃሚ ምክር • የንብ እርባታ ጣቢያ መጠን እንዳካባቢው የቀስም አይነትና ብዛት፣ የካፒታል መጠን፣ የስራ ቁሳቁስ እንዲሁም ባለው የተማረ የሰው ኃይል ሁኒታዎች ሊለያይ ይችላል። • ስለሆነም የንብ እርባታ ጣቢያ በምንመርጥበት ወቅት እነዚህን ነጥቦች ታሳቢ ማድረግ ይገባል። 17 2. ንፁህ ውኃ በአካባቢው ንፁህ ውኃ የሚገኝበት መሆን አለበት። ንቦች የእጭ ምግብ ለማዘጋጀትና በሙቀት ጊዜ ቀፎ ለማቀዝቀዝ ንፁህ ውኃ ያስፈልጋቸዋል። በተጨማሪም ውሃን ለንብ ቀሰም ዕፅዋት ልማት አገልግሎት ልንጠቀምበት እንችላለን። ስለዚህ ቀፎው ከተቀመጠበት በተወሰነ እርቀት ወንዝ፣ ኩሬ፣ ምንጭ፣ የሚንጠባጠብ የቧንቧ ውኃ ቢኖር ይመረጣል፤ እነዚህ የውኃ ምንጮች በሌሉበት አካባቢ አናቢው በበጋ ወራት በየቀኑ በገንዳ ንፁህ ውኃ ማቅረብ ይጠበቅበታል፣ 3. ተስማሚ የአየር ጸባይና የከፍታ መጠን ንቦችን ለማነብ የሚመረጠው ቦታ ተስማሚ የአየር ፀባይ ያለው መሆን አለበት፤ ውርጭና ከፍተኛ ሙቀት ያለበት ቦታ ለንብ ማነብ ተስማሚ አይደለም። ምክንያቱም፡- • በውርጭ ጊዜ አበባ ለመቅሰም ከቀፎአቸው ከመውጣት ይልቅ የቀፎውን የውሥጥ ሙቀት ለመጠበቅና እጩን ለመንከባከብ በመሰባሰብ ሙቀት እንዲጨምር ያደርጋሉ፣ • በሙቀት ወቅት ደግሞ ክንፋቸውን በማርገብገብና በማናፈስ ከእጩም ሆነ ከቀፎው አጠቃላይ የውስጥ ሙቀት እንዲቀንስና እንዲስተካከል ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ ውኃ በማምጣትና በቀፎው ውስጥ በመጨመር የቀፎውን የውስጥ ሙቀት ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ። ይህም ጊዜያቸውን ስለሚሻማ ምርታማነታቸውን ይቀንሰዋል። 4. ረግረጋማ ያልሆነ ቦታዉ ከረግረጋማና ከጎርፋማ ቦታዎች የራቀ መሆን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም እርጥበት አዘል የሆነ አካባቢ የሻጋታ መራባትን ያፋጥናል፣ ማር እንዳይበስልም ያደርጋል፣ እጭም ጊዜውን ጠብቆ እንዳይፈለፈል ያስተጓጉላል፣ 5. ከተለያዩ የንብ ጠላቶች ነፃ የሆነ (አነስተኛ ተፅዕኖ ያለው) 6. ከተለያዩ ንቦችን ከሚረብሹ (ድምፅ፣ ብክለት፣ ንዝረት፣ እንቅስቃሴ) ነገሮች የራቀ መሆኑ 7. በአካባቢው የንብ እርባታ መኖር 8. እሳት አደጋን ከሚያስነሱና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች የራቀ ለማናቢያ ጣቢያ ተስማሚ ያልሆኑ ቦታዎች • በብዛት የብዕር ሰብሎች የሚመረትበት (ስንዴ፣ ገብስ)፣ የሻይ እርሻ ልማት ቦታዎች • በበብዛት ፅድ የመሳሰሉ ጫፋቸው ቀጫጫን ዛፎች ያሉበት • መርዛማ ዕጽዋት ያሉበት አካባቢ • የኬሚካል ማከማቻ ወይም በብዛት የኬሚካል ርጭት የሚካሄድበት ቦታ • የእንስሳት ህክምና የሚሰጥበባቸው እና የመድሃኒት ማከማቻዎች • ከፍተኛ በካይ እና የኢንዱስትሪ ብክለት ያለበት ቦታ • ከፍተኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ያለበት ቦታ • የፍሳሽና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ/ማቃጠያ፣ መድፊያ ቦታዎች አካባቢ • የረጋ እና የተበከለ ውሃ 18 • የውሃ መጥለቅለቅ፣ የእሳት ወዘተ የመሳሰሉ አደጋዎች ያሉበት • በአጠቃላይ በአካላዊ፣ ስነ-ህይወታዊ እና ባህርያዊ አደጋ የሚያስከትሉ ሁሉ ለንብ ጣቢያ የማይመረጡ ናቸው። ማሳሰቢያ • የማናቢያ ቦታው ከት/ቤቶች፣ ልጆች ከሚጫወቱበት አካባቢ፣ ከገበያ ቦታዎች፣ ከህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ ከእንሰሳት እርባታ ጣቢዎች፣ ከመሳሰሉት ቢያንስ ከ400-500 ሜትር ራቅ ያለ መሆን ይኖርበታል፣ • ቀፎውን ከኃይለኛ ንፋስ መከላከል ያስፈልጋል፤ እንዲሁም ከፍተኛ የፀሀይ ጨረር እንዳያገኘው ማድረግ አስፈላጊ ነው፣ • ንቦችን በጓሮ አካባቢ የምናስቀምጥ ከሆነ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ሰውም ሆነ እንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ በዓይነ ብልጡ ፊት ለፊት ከሁለት ሜትር ርቀት በኋላ ሁለት ሜትር ከፍታ ያለው አጥር ማጠር አስፈላጊ ነዉ፣ • የንብ እርባታ ጣቢያውን መንከባከብ ማለትም አጥር ማጠር ፣ የንብ ጋጣና አልጋ መስራት፣ የመሸከም አቅሙን ማመጣጠን፣ የንቦች አቀማመጥ፣ አቅጣጫና ርቀት ማመጣጠን፣ የንቦችን ጤንነትና ደህንነት መከታተል እንዲሁም የጣቢያውን እና የቀፎውን ፅዳት መጠበቅ ያስፈልጋል። • የንብ እርባታ ጣቢያውን ውጤታማነት ለማሻሻል ውጤታማ የንብ እርባታ አካባቢ፣ እውቀትና ልምድን ማቀናጀት፣ የቀሰም ዕፅዋት የሚያብቡበትን ጊዜና ርዝማኔ ማወቅ፣ ምርታማ የሆኑ አዳዲስ የቀሰም ዕፅዋትን ወደ ጣቢያው ማስገባትና መንከባከብ እና የንቡን ምርታማነትና የጣቢያውን አጠቃላይ ውጤታማነት መገምገም ተገቢ ነው። የንብ ጋጣ እና የቀፎ ማስቀመጫ አሰራር ኅብረ ንቦችን በሚመቻቸው ቀፎ ውስጥ አድርጎ በተስማሚ ቦታ ከማስቀመጥ በተጨማሪ በንብ መጠለያ ወይም ጋጣ ውስጥ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። የንብ መጠለያ ማለት ንቦችን ከፀሐይ፣ ከብርድ፣ ከንፋስ፣ ከዝናብ እና ከልዩ ልዩ የንብ ጠላቶች የሚከላከል ነው። የመጠለያው ስፋት በኅብረ ንቦች ቁጥር የሚወሰን ሲሆን በአካባቢ ከሚገኙ ቁሳቁሶች በቀላሉ መሥራት ይቻላል። የቀፎ ማስቀመጫ ቀፎውን ከመሬት ከፍ አድርገን የምናስቀምጥበት አልጋ ነው። የቀፎ ማስቀመጫ የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት። • ቀፎውን ከመሬት እርጥበት፣ ቅዝቃዜ፣ ሙቀት እና ከጎርፍ አደጋ ይጠብቃል፣ • ንቦችን ከቁጫጭ፣ ጉንዳን እና ሌሎች የንብ ጠላቶች ይከላከላል፣ • ለንቦች መብረር (መውጣትና መግባት) ምቾትን ይሰጣል፣ • አናቢው በቀላሉ የቀፎ ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን እና ማር ለመቁረጥ ያመቻል። የቀፎ ማስቀመጫ የሚንቀሳቀስ ወይም መሬት ላይ የሚተከል ሆኖ መጠኑም አንድ ቀፎ ብቻ የሚያስቀምጥ ወይም ሁለት እና ከዚያ በላይ ቀፎዎችን እንዲያስቀምጥ ተደርጎ ሊሠራ ይችላል። የቀፎ ማስቀመጫው ከእንጨት፣ ከስሚንቶ፣ ከብሎኬት፣ ከብረት ወይም ከሌሎች ቁሳቁሶች በቀፎው ርዝመት እና ስፋት ተለክቶ የሚሠራ ሲሆን ከመሬት የሚኖረው ከፍታ ደግሞ 50 ሳንቲ ሜትር ወይም እስከ አናቢዉ ጉልበት ድረስ መሆን ይኖርበታል። 19 ምስል 7፡ ከእንጨት (ግራ)፣ ከብሎኬት (መሃል) እና ከብረት (ቀኝ) የተሰራ የቀፎ ማስቀመጫ የቀፎ ማስቀመጫ በምንሠራበት ጊዜ የሚከተሉት ነጥቦች ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው። • ጥንካሬው ቀፎውን፣ ኅብረ ንቦችንና በቀፎው ውስጥ ያለውን ማር መሸከም የሚችል መሆን አለበት፣ • ከእንጨት የሚሠራ ከሆነ እንጨቱ የበሰለ፣ በቀላሉ የማይበሰብስ እና ምስጥን መቋቋም የሚችል መሆን አለበት፣ • ቀፎው በአልጋው ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ ከወደ ዓይነ ብልጡ በኩል ከ1-2 ሳንቲ ሜትር ዝቅ ማለት አለበት፤ ይህም ቀፎው ውስጥ ውኃ ወይም ሌላ ነገር ቢፈስ በዓይነ ብልጡ ተንጠፍጥፎ እንዲወጣ ከማድረጉም በተጨማሪ ክብደት ያለውን ነገር ንቦች በቀላሉ ጎትተው እንዲያወጡት ይረዳቸዋል፣ • የቀፎ ዓይነ ብልጥ ወደ ምስራቅ (ፀሐይ መውጫ) አቅጣጫ ቢሆን ይመረጣል፣ ይህ ካልሆነ ዓይነ ብልጡን ወደ ሰሜንና ደቡብ አቅጣጫ አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል። • ለአናቢው አሠራር እንዲያመች እና የመስክ ንቦች ቀፎአቸውን በቀላሉ እንዲለዩት አንዱ ቀፎ ከተቀመጠበት የሌላው ቀፎ የሚኖረው ርቀት 1 ሜትር እና ከዚያ በላይ ቢሆን ይመረጣል። • የንብ ቀፎን ዓይነ ብልጡ በአንድ አቅጣጫ ሆኖ ከፊትና ከኋላ ደርድሮ ማስቀመጥ ከኋለኛ ላሉት የመስክ ላይ ንቦች እንቅሳቃሴ ላይ ጫና ይፈጥራል፤ ስለዚህ ንቦችን ከፊትና ከኋላ ደርድሮ ማስቀመጥ የግድ ከሆነ በሁለቱ ቀፎ መካከል የሚኖረው ርቀት 2 ሜትር እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት። 2.3. የቀሰም እፅዋት ልየታ እና ልማት የአበባ ሀብቶችን መለየት የአበባ ዘር አዳቃይ ነፍሳትን ጤናን ለማሳደግ እና የተሳካ የአበባ ዘር የማዳቀል ተግባርን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው። የአበባ ሀብቶች መገኘት በእድገት ወቅት ሁሉ ይለዋወጣል። ጤናማ ህብረ ንቦችን ለመደገፍ የተለያየ (ወቅታዊ) ፣ ረዥም መኖ (የኣበባ ወለላና ዱቄት) ማቅረብ አስፈላጊ ነው። የንብ ቀሰም እፅዋት ልየታ • እፅዋት የሚያድጉበትና የሚያብቡበት ጊዜያት ይለያያል። ሁሉም የማር ዕፅዋት እኩል የአበባ ወለላና ጽጌ ብናኝ የማመንጨት ወይም የማስገኘት ብቃት የላቸውም። ስለዚህ አናቢዎች የአካበቢያቸውን የማር እፅዋት ዓይነት፣ መጠንና ማበቢያ ወቅት የሚያሳይ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። 20 የአበባ ቀን መቁጠሪያ (Floral Calendar) የአበባው የቀን መቁጠሪያ ንብ አናቢዎች የንብ እርባታዎችን ከአበባ ወቅቶች ጋር በማጣጣም የማር ምርትን ማሳደግ ይችላሉ። ስለሆነም የአበባ የቀን መቁጠሪያ በንብ እርባታ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፣ ይህም ሁለቱንም ህብረ ንቡን እና ንብ አናቢዎችን ይጠቅማል። ጠቃሚነቱን እንመርምር፡ 1. ለህብረ ንብ፡- • የመኖ ማመቻቸት/ማመጣጠን፡ የማር ንቦች ማር እና የአበባ ዱቄት ለማምረት በአበባ ተክሎች የአበባ ማር ላይ ይመረኮዛሉ። የአበባው የቀን መቁጠሪያ የተወሰኑ ተክሎች ሲያብቡ በማመልከት መኖን ለማመቻቸት ይረዳቸዋል። በዚህ ጊዜ ንቦች በአበባው ወቅት የአበባ ወለላ በመሰብሰብ ላይ ማተኮር ይችላሉ። • ችግርን ማለፍ እና የተመጣጠነ ምግብ ማከማቸት፡ የአበባውን ቀን ማወቅ ንቦች በቂ ምግብ እንዲሰበስቡ ያስችላቸዋል። ዓመቱን ሙሉ በወለላ ማር የበለጸጉ አበቦችን ትኩረት አድርገው እንዲያገኙ ያረጋግጥላቸዋል። ይህም ህይወታቸውን እና አጠቃላይ ጤንነታቸውን ይደግፋል። • የህብረ ንብ እድገት፡ በጥሩ ሁኔታ የተስተካከለ የአበባ የቀን መቁጠሪያ ህብረ ንቦች በብቃት እንዲያድጉ ይረዳል። ንብ አናቢዎች በሚጠበቀው የአበባ ማር እና የአበባ ዱቄት አቅርቦት ላይ በመመስረት የንብ ቀፎ ሀብትን በዘዴ ማስተዳደር ይችላሉ። 2. ለንብ አናቢዎች፡- • የማር ምርት፡- ንብ አናቢዎች የንብ እርባታዎችን ከአበባ ወቅቶች ጋር በማጣጣም የማር ምርትን ማሳደግ ይችላሉ። የተወሰኑ ዕፅዋት ሲያብቡ በማወቅ አናቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ማር እንዲያመርቱ ያግዛል። • የአበባ ዘር ማዳቀል አገልግሎት፡- ንብ አናቢዎች ብዙ ጊዜ የአበባ ዘር የማዳቀል አገልግሎት ለመስጠት ቀፎዎቻቸውን ያከራያሉ። የአበባ ካላንደርን መረዳታቸው የንብ ቀፎዎችን ከሰብል አበባ ጋር እንዲያቀናጁ ይረዳቸዋል፣ ይህም የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ገበሬዎችን እና ንብ አናቢዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። • የንብ ጤና፡ የአበባውን የቀን መቁጠሪያ መከታተል ንብ አናቢዎች የህብረ ንቦቻቸውን ጤና እንዲገመግሙ ያስችላቸዋል። ንቦች በተወሰነ ወቅት እንደተጠበቀው የማይመገቡ ከሆነ፣ እንደ በሽታ ወይም የአካባቢ ጭንቀት ያሉ ጉዳዮችን ሊያመለክት ይችላል። • ንግሥት ማሳደግ፡ ንብ አናቢዎች በዓመታዊ የአበባ ማበብ ዘይቤ ላይ ተመስርተው ንግሥት የማሳደግ ሥራዎችን ጊዜ ሊያመቻቹ ይችላሉ። ይህ ወሳኝ በሆኑ ወቅቶች ጠንካራ ህብረ ንቦች መኖራቸውን ያረጋግጣል። 21 የአበባ ቀን መቁጠሪያን ማዘጋጀት በበርካታ አመታት ውስጥ ቀጣይነት ያለው መረጃ መሰብሰብ እና ጥሩ ማስተካከያን ያካትታል። ነገር ግን ፈጣን ደረጃዎች እነኚሁና፡ 1. የዳሰሳ ጥናት ማድረግ: በአካባቢዎ ያሉ የአበባ ተክሎችን ይዘርዝሩ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የአበባ ተክሎችን ትኩረት ይስጡ። 2. የህብረ ንቦችን ማኖር፡ ጠንካራ ህብረ ንቦችን በአቅራቢያ ያስቀምጡ እና በቀፎው ውስጥ የተከማቸ ምግብ ለውጦችን ይመልከቱ። 3. ቀኖችን መመዝገብ: ለተለያዩ ዕፅዋት የአበባ መጀመሪያ እና መጨረሻ ቀን ይመዝግቡ። ያስታውሱ፣ በጥሩ ሁኔታ የተስተካከለ የአበባ የቀን መቁጠሪያ ንቦችን እና ንብ አናቢዎችን ይጠቅማል፣ ይህም በነዚህ አስፈላጊ የአበባ ወለላና ዱቄቶች እና በሚንከባከቧቸው መካከል ተስማሚ የሆነ ግንኙነት ይፈጥራል። ለንብ የሚሆኑ የቀሰም እፅዋት አይነቶች  ንቦች እንደማንኛውም እንስሳት ለመኖርና ለመራባት መኖ ያስፈልጋቸዋል። ለንቦች መኖ የሚያስገኙ እፅዋት ሁሉ የቀሰም (ማር) እፅዋት ይባላሉ። እነዚህም ለንቦች መኖና ለማር ማዘጋጃ የሚሆኑ የአበባ ወለላ (ቀሰም) እና ጽጌ ብናኝ (ድኝ) ወይም ከሁለቱ አንዱን የሚያስገኙ የሚያብቡ እፅዋት ናቸው። አገራችን ባላት መልከአ ምድራዊ አቀማመጥና ተስማሚ የአየር ንብረት በርካታ የማር እፅዋት ዓይነቶች አሏት። እስካሁን ድረስ በተካሄደ ጥናት ከስምንት መቶ በላይ የማር እፅዋት ዓይነቶች ተለይተው ታውቀዋል። በአገራችን የተሻለ የማር ሰጪነታቸው ከሚታወቁት መካከል ግራር፣ ዋንዛ፣ ገተም፣ አስታ፣ ባህር ዛፍ፣ መንጠሴ (ተበብ)፣ የአደይ አበባ፣ ማገጥ፣ ቅባት እህሎች፣ ግራዋ፣ ኮሸሽሌ የመሳሰሉት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።  ሁሉም የማር ዕፅዋት እኩል የአበባ ወለላና ጽጌ ብናኝ የማመንጨት ወይም የማስገኘት ብቃት የላቸውም። አንዳንድ የማር እፅዋት ከፍተኛ የአበባ ወለላ አመንጪዎች ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ በመጠኑ ያመነጫሉ፤ ሌሎቹ ድገሞ ጽጌ ብናኝ በብዛት ሊስጡ ይችላሉ፣ ሁለቱንም የሚያስገኙት የማር እፅዋትም እንዳሉ ይታወቃል።  የማር እፅዋት የሚያድጉበትና የሚያብቡበት ጊዜያት ይለያያል። ስለዚህ አናቢዎች የአካበቢያቸውን የማር እፅዋት ዓይነት፣ መጠንና ማበቢያ ወቅት የሚያሳይ ካሌንዳር ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። 22 ሠንጠረዥ 2: የዋና ዋና የቀሰም እጽዋት የማበቢያ ቀን ሰሌዳ No የዋና ዋና የቀሰም እጽዋት የማበቢያ ቀን ሰሌዳ Flowering calendar of the major bee plant species ምርመራ የአበባው ዓይነት Flowering species የሚሰጠው Source (pollen/nectar /both) የማበቢያ ጊዜ/ወር (ከጅምር እስከ ፍጻሜ) Flowering time/month (start to end) Remarks , if any ሳይንሳዊ ስም Scientific Name አካባቢያዊ ስም Local Name Jan Feb Mar Apr May Jun Jul Au g Se p Oct No v De c A Pulses 1 Cicer arietinum L. Shumbura/shimbira Nectar 2 Glycine max (L.) Merr. Akuri ater Nectar 3 Lathyrus sativus L. Gaya/Guaya Nectar 4 Lens culinaris Med. Misira/Misir Nectar 5 Phaseolus vulgaris L. Adenguare Nectar 6 Pisum sativum L. Atara/Ater Nectar 7 Vicia faba L. Bakela/Bakela Nectar B Cereal 1 Zea mays Boqooloo/Boqolo Pollen 2 Sorghum bicolor (L.) Mishinga/Mashila Pollen B Oil seed 1 Brassica carinata A. Br. Gomanzara/Gomenz er Both 2 Guizotia abyssinica (L. Fil.) Cases Noug/Noug Both 3 Linum usitatissimum Linn. Talba/Telba Both 4 Vigna radiata Masho/Masho Both 5 Sesamum indicum Sinsina/Salix Both 6 Ricinus communis L. Kobo/Gulo Both 7 Carthamus tinctorius L. Sufi/Suf Both 8 Nigella sativa Abshuda guracha/xiqur azimud Both 23 9 Coriandrum sativum) Dinbilaala/Dimbilal Both 10 Trigonella foenum- graecum L. Shuqo/Abish Both C Roots and Tubers 1 Solanum tuberosum L. Dinicha/Dinch D Spices and condiments 1 Capsicum frutescens L. Barbare/Berberie Nectar 2 Rhamnus prinoides L'Herit Gesho Pollen 3 Ruta chalepensis L. Tenaadami/Tenaada m Both E Stimulants 1 Catha edulis (Vahl.) Forssk. ex. Endl. Jima/Chat 2 Coffea arabica L. Buna/Kawa/Bunaa Both 3 Nicotiana tobacum L. Timbo/Timbaho Pollen F Vegetables 2 Lycopersicon esculentum Mill. Tmatiim/Timantim Pollen 3 Saccharum officinarum L. Shankora agda/Shenkora ageda Pollen G Fruits 1 Carica papaya L. Papaya/Papaya Both 2 Citrus sinensis (L.) Osheck. Birtukana/Birtukan Both 3 Citrus aurantifolia (Christm.) Wingle Lomi/Lomi Both 4 Mangifera indica L. Mango/Mango Both 5 Musa x paradisiaca L. Muzi/muz Both It is a year- round 24 crop. 6 Persea americana Mill. Avokado/Avokado Both 7 Psidium guajava L. Zaytuna/Zeyitu Both 8 Malus sylvestris Barnchy Pome/pome Both H Tree and shrub species 1 Carissa spinarum L. Hagamsa/Agam Both 2 Casuarina cunninghamiana Miq. Shawshawe/Arzeliba nos Both 3 Cordia africana Lam. Wadesa/wanza Both 4 Croton macrostachyus Hochst. ex Del. Bakanisa/Bisana Both 5 Eucalyptus globulus Labill. Bargamo adi/Nech bahr-zaf Both 6 Hagenia abyssinica (Bruce) J.F. Gmel. Heto/Kosso Both 7 Rubus apetalus Poir. Gora/Enjori Both 8 Acacaia albida Del Garbi /Girar Both 9 Acacia senegal (L.) Willd. Sapesa/kontir Both 10 Dovyalis abyssinica (A. Rich) Warb. Koshami/koshim Both 11 Erythrina brucei Schweinf walensu/korch Both 12 Eucalyptus camaldulensis Dehn Bargamo dima/Key Bahr-zaf Both 13 Euphorbia candelabrum Trem. & Kotschy. Adami/Kulkuwal Both 14 Justicia schimperiana (Hochst. ex Nees) T. Anders. Umuga/sensal Both 15 Lippia adoensis Hochst. ex Wal sukaye/kasse Both 25 16 Melia azedarach L. Nim/nim Both 17 Moringa stenopetala (Bak.) Cuf. Shiferaw/alako Nectar 18 Ocimum gratissimum L. Bokol/Damakase Nectar 19 Olea europaea L. subsp. Cuspidata (Wall. ex G.Don) Cif. Ejersa/wayira Nectar 20 Podocarpus falcatus (Thunb.) Mirb Birbirsa/Zigba Nectar 21 Rhamnus prinoides L' Herit Geshe/Gesho Nectar 22 Sesbania sesban (L.) Merr Incini/sasbania Pollen 23 Vernonia amygdalina Del. Ebicha/Gerawa Both 24 Acacia mellifera Bilala Both 25 Millettia ferruginea Birbiraa/Birbira Both 26 የንብ ቀሰም እፅዋት ልማት ፈጥነው በማደግ የሚያብቡ የማር እፅዋትን ማልማትና መንከባከብ • በአሁኑ ወቅት በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የአገሪቱ የማር ማምረት አቅምና እፅዋት ክምችትና ስርጭት እየተመናመነ በመሄድ ላይ ይገኛል። በተለይ ዝግባ፣ ዋንዛ፣ አስታ፣ ሎል፣ የመሳሰሉ አገር በቀል እፅዋቶች ለልዩ ልዩ አገልግሎት እየተቆረጡ በመጥፋት ላይ ናቸው። ይህንን አዝማሚያ ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ ተግባራት ዋነኛው የማር እፅዋት ሃብታችንን መጠበቅና አዳዲስ የማር እፅዋትን ማልማት ነው። • አናቢዎች ኅብረ ንቦችን ባስቀመጡበት አካባቢ የበቀሉ የማር እፅዋትን ከመንከባከብ በተጨማሪ መሬት ያላቸው ከሆኑ ፈጥነው በማደግ ቶሎ የሚያብቡ የማር እፅዋት ዝርያዎች ማልማት ይጠበቅባቸዋል። እንዲሁም ደግሞ ለንቦችም ሆነ ለእንስሳት ጥቅም የማይሰጡ (መርዛማ የሆኑ) እፅዋትን መቁረጥና በምትካቸው ንቦች የሚፈልጓቸው ሌሎች ዘርፈ ብዙ እፅዋትን ማልማት ያስፈልጋል። • የንብ ማነብ ስራ በእፅዋት ላይ ጉዳት ሳያስከትል በጓሮ፣ ደንና የተራቆቱ ቦታዎችን በእፅዋት በመሸፈን የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል ከሚከናወነው የዛፍ ተከላና የአፈርና ውኃ ልማትና ጥበቃ ስራ ጋር በማቀናጀት በተጓዳኝ ሊሠራ ይችላል። የማር እፅዋትን መትከልና ማልማት ለንቦች ተጨማሪ መኖ ያስገኛል። የንብ ማናቢያ ቦታው በዋና የማር ወቅት የሚያብቡና ከማር ምርት በኋላ የሚያብቡ የማር እፅዋት የሚገኙበት አካባቢ ከሆነ በእጅጉ ተመራጭ ያደርገዋል። ምክንቱም ንቦች በተለያዩ ጊዜያት ለምግባቸው የሚሆኑ አበባ ስለሚያገኙ ነው። • በብዙ የአገራችን ክፍሎች የንቦች መኖ እጥረት የሚጋጥመው ከታህሳስ መጨረሻ እስከ ሚያዝያ ባለው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ በእነዚህ ወራት ሊያብቡ የሚችሉ (ባህር ዛፍ፣ ግራዋ፣ ደንገሪታ፣ ዶቅማ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ኮሸሽሌ፣ እሬት፣ ቃጫ የመሳሰሉትን) የማር እፅዋትን መርጦ መትከል ወይም ማልማት ንቦች ሳይጎዱ ለሚቀጥለው የማር ወቅት እንዲደርሱ ያደርጋል። በዚህ አይነት የተጠናከሩ ንቦች ከፍተኛ ማር ለመስራትና ለማከማቸት ይችላሉ። ስለሆነም አናቢዎች በሚኖራቸው ቦታ ሊያለሙ የሚችሉትን እፅዋት ቢተክሉ ጠቃሚነቱን የጎላ ይሆናል፤ እንዲሁም በአፈር በዝናብና በነፋስ መሸርሸርን ለመቆጣጠር የሚሰሩ እርከኖችና ቦታዎች የሚተከሉ ዛፍ አይነቶች ለንቦች ምግብ ቢሆኑ ይመረጣል። ማሳሰቢያ ለንብ ቀሰም የሚሆኑ ዕፅዋትን ለሚያለሙና ችግኝ በማዝጋጅት ለሚሳተፉ ኢንተርፕራይዞች ለችግኝ ዝግጅት አስፈላጊ ግብዓት ከማዘጋጀት ጀምሮ ሰለ መሬት/መደብ ዝግጅት፣ ችግኝ አዘገጃጀት፣ ልማትና እንክብካቤ ላይ ጥልቅ ስልጠና እንደሚሰጥ ታሳቢ ይደረግ። 27 ክፍል 3፡ ህብረ ንቦችን ማዛወርና መንከባከብ 3.1. ህብረ ንቦችን ማጥመድና ማዘዋወር ህብረ ንቦችን ማጥመድ ንቦችን ከሰፈሩበት ቦታ መያዝ (ማጥመድ) ኅብረ ንቦች ከነበሩበት ቀፎ ወልደውም ሆነ በተለያየ ምክንያት በሚወጡበት ጊዜ በአቅራቢያ ከሚገኘው ዛፍ ቅርንጫፍ ወይም አጥር ላይ በመስፈር የሚሄዱበትን ቦታ (ቀፎ) በአሳሽ ንቦች በመታገዝ ከለዩ በኋላ የነበሩበት የንብ ቀፎና አካባቢ ለመጨረሻ ጊዜ ለቀው ይሄዳሉ። ንብ አናቢው ይህን ጊዜ በመጠቀም ንቦችን ወደ ሌላ ቀፎ በመገልበጥ ለማስቀረት ብዙ ጥረቶች ማድረግ ይጠበቅበታል። በመሆኑም አንድ ንብ አናቢ ምንጊዜም ቢሆን በንብ ጋጣው ውስጥ ያለውን የኅብረ ንብ ብዛት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተዘጋጁ ባዶ ቀፎዎች ሊኖሩት ይገባል። በተጨማሪም የተወለዱ ወይም የሚኮበልሉ ንቦች የሚያርፉበት የቀሰም እፅዋት ዛፍ በቀፎ ማሰቀመጫው ቦታ ዙሪያ መትከል ይጠበቅባቸዋል። ከቀፏቸው በዚህ ምክንያት የወጡ ንቦችን ማስቀረት የሚቻለው አዲስ ቦታ ለመምረጥ የሄዱት አሳሽ ንቦች ከመመለሳቸው በፊት መሆን ይገባዋል። በመሆኑም ንቦች ከነባሩ ቀፎ ወጥተው ከሰፈሩበት ስፍራ ላይ ውኃና ጭስ በመጠቀም ኀብረ ንቡን ሊይዝ የሚችል ንፁህ ካርቶን ወይም የስፌት እቃ (ወስከንቢያ ወይም ቁና) በመጠቀም ንቡን ወደ ካርቶኑ ወይም ስፌቱ ውስጥ በማራገፍ እንዲረጋጋ በማድረግ እናት ንብን መፈለግ ያስፈልጋል። እናት ንብ በሚፈለግበት ጊዜ ንቦች የመናደፍ ዝንባሌ ስለሌላቸው በተቻለ መጠን ጭስ ከመጠቀም ይልቅ ውኃ በቀላሉ መርጨቱ የንቦችን ክንፍ እንዳይበሩ ስለሚያደርገው እናት ንብን ፈልጎ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። እናት ንብ ከተያዘች በኋላ በእናት ንብ መያዣ ወይም ቁፍጣን ውስጥ በማስቀመጥ ኅብረ ንቡን ወደሚፈለገው ቦታ ማጓጓዝና በቀፎ ውስጥ በማስቀመጥ እንዲላመዱ ማድረግ ይቻላል። ኅብረ ንቦችን ቀፎ በመስቀል ማጥመድና መያዝ ለንቦች ማጥመጃ የሚሆነው ቀፎ በደንብ የተሠራና ንቦችን ሊስብ በሚችል ጥሩ ጠረን ባለው አባሎ፣ ሎል፣ ወይራ በመሳሰሉት እፅዋት የታጠነና ውስጡ በደረቅ የማር እንጀራ ወይም ሰም የታሸገ ቢሆን ንቦችን በተሻለ መልኩ ሊስባቸው ይችላል። ለንቦች ማጥመጃ የሚሆነውን ቀፎ ከላይ በተዘረዘረው መንገድ ከተዘጋጀ በኋላ በአካባቢው በሚገኙ ትላልቅ ዛፎች ላይ አበባ በብዛት በሚያብብበትና የንቦች የእድገት ዑደት በሚጀምርበት ወቅት መስቀል ይቻላል። ይህ አሰራር አዲስ ንብ አናቢዎችም ሆነ ልምድ ያላቸዉ አናባዎች ኅብረ ንባቸውን ለማስፋት ለዘመናት ሲጠቀሙበት የቆየ ብቸኛው መንገድ ነው። ሆኖም በጫካ ውስጥ የሚገኙ ንቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከደን መጥፋት ጋር ተያይዞ እየተመናመኑ በመምጣታቸው ንቦችን አጥምዶ የመያዝ ዕድሉ አነስተኛ ነው። 28 ህብረ ንቦችን ማዘዋወር ኅብረ ንቦችን ከአንድ ቀፎ ወደ ሌላ ቀፎ ማሸጋገር በባህላዊ ቀፎ ያሉትን የማነብ ችግሮች ለማስወገድና የተሻለ የማር ምርት ለማግኘት ንቦችን ወደ ሌላና አዲስ ቀፎ ማሸጋገር ወይም ማዛወር ይቻላል። ኅብረ ንብ መቼና እንዴት ይሸጋገራል? ኅብረ ንቦች ከአንዱ ቀፎ ወደ ሌላ ቀፎ በተለይም ከባህላዊ ቀፎ ወደ ባለርብራብ ወይም ባለፍሬም ቀፎ የሚሸጋገሩበት ዋነኛ ዓላማ ለቀፎ ክትትልና ቁጥጥር እንዲመች እንዲሆን፣ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት እና ሌሎች የንብ ውጤቶችን ለማምረት አመቺ ስለሆነ ነው። ኅብረ ንቦች ከአንዱ ቀፎ ወደ ሌላ ቀፎ የሚሸጋገሩበት ወቅት ከቦታ ቦታ ሊለያይ ስለሚችል ትክክለኛ ጊዜውን ለማወቅ የቀበሌውን ነባር አናቢዎች ወይም የእንስሳት ልማት ባለሙያዎችን መጠየቅና መረዳት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ነገር አንድ ወጥ የሆነ የማሸጋገሪያ ጊዜ በሁሉም አካባቢ አይኖርም። የኅብረ ንቦች ማሸጋገሪያ ወቅት የሚወሰነው በአካባቢው ባሉት የቀሰም እፅዋቶች የአበባ ጊዜ ይሆናል። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ፣ • በደጋማ አካባቢዎች፡ የበልግ ዝናብ ከዘነበ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ሃምሌ ድረስ ሲያሸጋግሩ አንዳንዶቹ ደግሞ በመስከረም ወር ያሻግራሉ። • በወይና ደጋና በቆላማ አካባቢ አበባ አብዛኛውን ጊዜ ሊኖር የሚችለው የመኸሩን ዝናብ ተከትሎ ስለሆነ ከነሀሴ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ ይሆናል። ኅብረ ንቦችን ለማሸጋገር የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ንቦችን ከባህላዊ ወደ ርብራብ ወይም ወደ ባለፍሬም ቀፎ ለማሸጋገር የሚከተሉት ማናቢያ መሣሪያዎች / ቁሳቁሶች ያስፈልጋሉ። • ጠንካራ ኅብረ ንብ የያዘ ባህላዊ ቀፎ፣ • የተዘጋጀ የፍሬም ቀፎ ወይም የርብራብ ቀፎ፣ ርብራቦች በሰም መቀባት አለባቸው፣ • የማናቢያ ትጥቆች (ዓይነ ርግብ፣ ቱታ፣ ጓንት፣ ቦት ጫማ፣ ማጨሻ) • ለጭስ የሚሆን የቃጫ ኬሻ፣ ቆረቆንዳ፣ የገብስ ገለባ፣ የጤፍ ጭድ፣ • የውኃ መርጫ (ውኃ ንቦች ላይ በመርጨት እንዳይበሩ ለማድረግ) • ቢላዋ (ከባህላዊው ቀፎ የማር እንጀራ ለመቁረጥ) ፣ • ብሩሽ ወይም ሙሬ (ከሚቆረጠው የማር እንጀራ ላይ ንቦችን ለመጥረግ) • የሰሌን ወይም የሸራ ምንጣፍ (ንቦች ከባህላዊው ቀፎ ሲዛወሩ መሬት ላይ እንዳይወድቁ የሚነጠፍ)፣ • ሰፊ ሳህን ወይም ትሪ ከነክዳኑ (የሚቆረጠውን የማር እንጀራ ለማስቀመጥ)፣ • ቀጭን ሲባጎ፣ ገመድ ወይም ጠንከር ያለ የሳር አይነት - ግራንጣ (ወደ አዲሱ ቀፎ የምናስገባውን ማር፣ የአበባ ዱቄትና እጭ የያዘውን የማር እንጀራ በአዲሱ ቀፎ 29 • ከተዘጋጀው ፍሬም ወይም ርብራብ ጋር ለማሰር)፣ • ባትሪ ለመብራት፣ • የንግሥት ንብ ማያዣ ሣጥን፣ • ንፅህ ውኃ በጣሳ እና ማር ወይም ስኳር፣ • የገብስ ገለባ ወይም ደረቅ ሣር፣ • ቀፎ ለማሸት የሚያገለግል መልካም መዓዛ ያለው ዕፅዋት። ኅብረ ንቦችን ከባህላዊ ቀፎ ወደ ርብራብ ቀፎ የማሸጋገር ሂደት • ንብ ለማዛወር የምንጠቀምበትን ቦታ ማጽዳትና የሰሌን ወይም የሸራ ምንጣፍ ማንጠፍ፣ • ባህላዊውን ቀፎ በርብራቦች ወይም በሌላ እንጨት አስደግፎ ግማሽ ጫፉን ወደ አዲሱ ቀፎ ማስገባት ወደ ቀፎው የገባው ጫፍ ከፍቶ በሌላኛው ጫፍ ጭስ ማጨስ፣ • በምንጣፍ የላይኛው ጫፍ ንብ የሚዛወርበትን የርብራብ ቀፎ ዓይነ-ብልጡን ፊት ለፊት በማድረግ ማስቀመጥ፣ • ንብ የያዘውን ባህላዊ ቀፎ ቀስ አድርጎ በታችኛው የምንጣፍ ጫፍ ማስቀመጥ፣ በአንድ በኩል (በሰፊው በኩል) በመክፈት በንቦች ላይ ጭስ ማጨስ፣ • በመጀመሪያ ንቡ የለቀቀውን የማር እንጀራ ቆርጦ በትክክል ከርብራቡ ላይ ማሰርና አዲሱ ቀፎ ውስጥ ማስቀመጥ፣ • አልፎ አልፎ ጭስ እያጨሱ እጭና ማርን እየቆረጡ ከርብራቡ ላይ ማሰር፣ • ከአሮጌው ቀፎ እጭና ማር ካልተገኘ ማር ወይም ስኳር በንጹህ ውኃ በጥብጦ በጣሳ ማስቀመጥ፤ ንቦች ውኃው (ውህዱ) ውስጥ ገብተው እንዳይሞቱ ለመወጣጫ የሚሆናቸው የገብስ ገለባ ወይም ደረቅ ሣር መጨመር፣ • በጭሱ አማካኝነት ንግሥት ንብ ወደ አዲሱ ቀፎ (እጭና ማር ወደ ታሰረበት ርብራብ ቀፎ) ከገባች ቀሪው ንብ እሷን ተከትሎ ይገባል፣ • ንቦች በአዲሱ ቀፎ ውስጥ ከገቡ በኋላ የቀፎውን ክዳን በአግባቡ መክደንና በተዘጋጀው የቀፎ ማስቀመጫ ላይ ማስቀመጥ፣ • በመጨረሻ አሮጌውን ቀፎ በደምብ አራግፎ ተመልሰው እንዳይገቡበት ንቦች ከማይደርሱበት ቦታ ማስቀመጥ (ለሌላ ጊዜ ማጥመጃ ሊሆን ይችላል) ፣ • ንቦች እስከ ሚለምዱና የራሳቸውን ምግብ ማዘጋጀት እስከ ሚጀምሩ ድረስ ማር ወይም ስኳር በውሃ እየበጠበጥን በየቀኑ ልንሰጣቸው ይገባል፣ • ንቦች የራሳቸውን ምግብ ማዘጋጀት ሲጀምሩ በቀፎው ውስጥ የሚቀመጥላቸውን ምግብ ስለሚተውት በዚህ ጊዜ ምግብ ማስቀመጡን ማቋረጥ ይቻላል፣ ኅብረ ንብ በሚገለበጥበት ጊዜ ስለ ኅብረ ንቡ ይዘት በጥንቃቄ መረዳት ያስፈልጋል። ኅብረ ንቡ ሲዛወርም ነባሩንና በጣም የጠቆረውን የማር እንጀራ ቆርጦ በማዉጣት አቅልጦ ወደ ሰም መቀየር ይቻላል። የማር እንጀራው በሙሉ ማር ሆኖ ከተገኘ ወደ አዲሱ ቀፎ አስሮ ማስገባቱ ከክብደቱ የተነሳ ከቀፎው ውስጥ ወድቆ ንቦችን ሊጎዳ ስለሚችል በቀጥታ ማምረቱ ይመረጣል። ሙሉ እጭና ያስታውሱ!  ከባህላዊው ቀፎ የተቆረጠው የማር እንጀራ ርብራቡ ላይ በሚታሰርበት ጊዜ ባህላዊው ውስጥ በነበረበት አቀማመጥ መሆን ይኖርበታል - መዘቅዘቅ የለበትም፤ ያለበለዚያ እጩ ይሞታል ንቦቹም አይለምዱም። 30 ግማሽ እጭ ግማሽ ማር የሆነውን እንጀራ ደግሞ ማሰርና ቀፎው ውስጥ ማስቀመጥ ተገቢ ነው። ምስል 8፡ ባህላዊ ቀፎ ውስጥ ያለ ኅብረ ንብን ወደ ርብራብ ቀፎ ሲዛወር ንቦችን ከባህላዊ ቀፎ ወደ ፍሬም ቀፎ ማሸጋገር ይህ ተግባር በርብራብ ቀፎ ለማሸጋገር እንደተዘረዘረው ሆኖ የሚለይበት የአሰራር ዘዴ በፍሬም ቀፎው ውስጥ ፍሬሞችና ከፍሬሙ ጋር የተያያዘ በሰው ሠራሽ መንገድ የታተመ እንጀራ ስለሚኖረው ከባህላዊ ቀፎ ያሉትን የማር እንጀራዎች ሙሉ በሙሉ ልናስገባ አንችልም። ሆኖም ከባህላዊው ቀፎ ያገኘናቸውን የተሻሉ እጭ የያዙ እንጀራዎችን በመምረጥ ከሶስት እስከ አራት የሚሆኑ ፍሬሞች ላይ በማሰር ከባለፍሬሙ ቀፎ ውስጥ መሀል ላይ በማስቀመጥ ኅብረ ንቡ በቀላሉ እንዲለምድ ማድረግ ይችላል። በዚህ መልኩ የገባውን እጭ የያዘ የማር እንጀራ ንቦች ከተላመዱ በኋላ በማውጣት የተጋገረ የሰም እንጀራ በተያያዘባቸው አዲስ ፍሬሞች መተካት ያስፈልጋል። ምስል 9: አናቢ ንብዎች ከባህላዊ ወደ ሽግግር ቀፎ ሲያዛውሩ እና ከተዛወሩ በኋላ በአደን የተያዙ ኅብረ ንቦችን ማሸጋገር በአደን የተያዘ ኅብረ ንብ በመጠናቸው ብዙ ጊዜ አነስተኛ ሊሆኑ ስለሚችሉ በተያዙበት ቀፎና በአረፉበት ቦታ ለአስር ቀን ያላነሰ ጊዜ ቢቆዩ ቀፎውን የበለጠ መልመድ ይችላሉ። እነዚህን ንቦች ለማሸጋገር ካስፈለገ ሊታሰር የሚችል የማር እንጀራ ላይኖራቸው ስለሚችል ከሌላ ቀፎ የማር እንጀራ በማውጣት ወደ ሚሸጋገሩበት ቀፎ በማሰር ማስገባት ያስፈልጋል። የሚደረግላቸው የማር 31 እንጀራ ያልጠቆረና እጭ ያለው ቢሆን ይመረጣል። ለተዛወሩት ንቦች ለዕለት ቀለባቸው የሚሆን የማር እንጀራ ማስገባቱም የመልመድ እድላቸውን ያሰፋዋል። ከተዘዋወሩ በኋላ መደረግ ስለሚገባዉ ጥንቃቄ ህብረ ንቡ አዲሱን ቀፎ እንዲለምዱ ጥሩ ሽታ ባላቸው ዕፅዋት ማሸት፣ ማጠን እንዲሁም ንፁህ ማድረግ ያስፈልጋል፣ በማንኛውም አጋጣሚ እናት ንብ ልትጎዳ ወይም ልትሞት ስለምትችል ጥንቃቄ ማድረግ፣ እንዲሁም ሰራተኛ ንቦች እንዳይሞቱ ወይም እንዳይጎዱ እንዲሁም በየቦታው ተበታትነው እንዳይቀሩ መጠንቀቅ ያሻል፣ ኅብረ ንቦች ወደ አዲሱ ቀፎ ከተዛወሩ በኋላ ጥለው እንዳይሄዱ ቢያንስ ለ3 ቀናት ያህል መጠበቅና ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። ንቦች ከተዛወሩ በኋላ ቀፏቸውን ለቀው ለመሄድ ሙከራ ካደረጉ መደረግ የሚገባው እናት ንቧን ፈልጎ በጥንቃቄ መያዝና በእናት ንብ መያዣ በማስቀመጥ ወደ ቀፎው በመመለስ ኅብረ ንቡ ተመልሶ ወደ ቀፎው እንዲገባ በማድረግ ነው። እናት ንብን እስከ ሶስት ቀን በተያዘችበት ሁኔታ በማቆየትና ክትትል በማድረግ ንቡ ቀፎውን ሊለምደው ይችላል። ከዚህ በኋላ እናት ንብን ከመያዣው መልቀቅና ነጻ እንድትሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የምናደርጋቸውም ክትትሎች የመስክ ንቦች እንደወጡ ከቀፎው እርቀው መሄዳቸውን፤ ከመስክ ተመላሽ ንቦች ደግሞ ቀሰም ማስገባታቸውን፤ የቀኑ ፀሐይ ሞቅ ሲል የሚወጡና የሚገቡ ንቦችን መጠን በመመልከት ንቦች አዲሱን ቀፎ መልመድና አለመልመዳቸውን አመላካች ሁኔታዎችን መገንዘብ ይቻላል። የተዛወሩት ንቦች በአዲሱ ቀፎ ውስጥ መልመዳቸው የሚረጋገጠው በቀፎው የማር እንጀራ ላይ የአበባ ወለላና ጽጌ ብናኝ ማከማቸት ሲጀምሩና እናት ንብ እንቁላል ጥላ እጭ ማደግ ሲጀምር ነው። የቀፎ ቁጥጥር ማካሄድ ወደ ተሻሻለ ቀፎ የተዛወሩ ንቦች የሚያከናውኗቸውን ተግባራት እየተከታተሉ በማየት ያሉባቸውን ችግሮችና የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ለማወቅ በየጊዜው የቀፎ ፍተሻ ወይም ቁጥጥር ማድረግ ያስፈልጋል። የቀፎ ቁጥጥርን በሁለት መልክ ከፍሎ ማየት ይቻላል። ሀ) ውጫዊ ቁጥጥር  ይህ አይነቱ ቁጥጥር በየቀኑ ጠዋትና ማታ ሊደረግ የሚችል ተግባር ነው፣  በውጫዊ ቁጥጥር የኀብረ ንቡን አጠቃላይ ውጫዊ ሁኔታ ማየት ይቻላል፤ የንብ ጠላቶችን እንደ ሸረሪት፣ እንሽላሊት፣ ቁጫጭ፣ ጉንዳን፣ ዘመሚት ያሉትን ነገሮች ማየትና ማስወገድ ያስፈልጋል፣  በቀፎ አይነ ብልጥ አካባቢ ችግሮች ካሉ፣ የበቀሉ አረሞችና አንዳንድ መሠናክሎች ካሉ ማጽዳት ያስፈልጋል፣  ብዙ ጊዜ በዚህ ዓይነት ቁጥጥር የመከላከያ አልባሳቶች ላያስፈልጉ ይችላሉ፣  በውጫዊ ቁጥጥር ማር መድረሱን አካባቢው ከሚኖረው ሽታ ማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን ንቦችን የሚጎዳ የኬሚካል ርጭት በአካባቢው ካለም በዓይነ ብልጡ ሞተው ከሚገኙት ንቦች 32 ሁኔታ በመነሳት ማወቅ ይቻላል።  የውጫዊ ቁጥጥር ስራ ስናካሂድ ከምናያቸው ምልክቶች በመነሳት የውስጥ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልካች ሁኔታዎችን በመጠቀም ውሳኔዎች ላይ ልንደርስ እንችላለን። ለ) ውስጣዊ ቁጥጥር ውስጣዊ ቁጥጥር ማለት የንቦችን ቀፎ በመክፈት በቀፎው ውስጥ ያለውን የንቦች እንቅስቃሴ መመልከትና መገምገም ነው። ወስጣዊ ቁጥጥር ከውጫዊ ቁጥጥር ግምገማ በመነሳት እንደ አስፈላጊነቱ ሊካሄድ ይችላል። በተደጋጋሚ ያላግባብ ቀፎን መክፈት ንቦችን ከመረበሽና ሥራቸውን ከመጉዳቱም በተጨማሪ በወቅቱ ልናገኝ የምንችለውን የማር መጠንም ሊያሳንስብን ይችላል። ስለዚህ ይህ ተግባር የመጀመሪያው የውስጥ ቁጥጥር ከተደረገ በኋላ የሚቀጥለው ቁጥጥር ሊደረግ የሚችለው የጊዜ ልዩነት ከ10 ቀን ማነስ የለበትም። ይህ የውስጥ ቁጥጥር በሚካሄድበት ጊዜ ሙሉ የንብ ንድፋት መከላከያ ትጥቅ መልበስና ጭስ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህ ተግባር ሰዎችና እንስሳት በሚኖሩበት አካባቢ ከሆነ በማታ ቢካሄድ ይመረጣል። የውስጥ ቁጥጥር ከተደረገ በኋላ ችግሮች ካሉ በአፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው። ውስጣዊ ቁጥጥር ስናካሂድ የሚከተሉትን ነገሮች ለማረጋገጥ መሆን አለበት። • ንግሥት ንብ መኖርና አለመኖሯን ለማወቅ፣ • የንቦችን ጤንነት (በሽታ) ሁኔታን ለማየት፣ • ለኀብረ ንቡ በቂ ቦታ መኖርና አለመኖሩን ለማረጋገጥ፣ • ለንብ የእድገት ኡደት የሚያበቁ ሁኔታዎች መኖርና አለመኖርን ለማየት፣ • በቂ የሆነ የተቀመጠ ማርና ጽጌ ብናኛ መኖሩን ለማረጋገጥ ነው። 3.2. ለኅብረ ንቦች የሚደረግ እንክብካቤ አናቢዎች ከንቦች የሚጠበቀውንና የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ወቅቱን የጠበቀ አያያዝና እንክብካቤ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የሚከናወኑት ተግባራት ኅብረ ንቦች በሚራቡበት (በሚዋለዱበት) ወቅት፣ በማር ወቅትና በድርቅ ወቅት ስለሚለያዩ ቀጥሎ በዝርዝር ቀርበዋል። ኅብረ ንቦች በሚራቡበት ወቅት የሚደረግ እንክብካቤ ይህ ወቅት በአካባቢዉ የቀሰም እፅዋት ማበብ የሚጀምሩበት ጊዜ በመሆኑ አናቢዎች ባዶ ቀፎዎችን በማፅዳት፣ በማጠንና አሮጌ የማር እንጀራዎችን በመቁረጥ የቀፎ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው። ከዚህ በኋላ ኅብረ ንቦች በሚዋለዱበት ወቅት የሚከናወኑ ተግባራት የሚከተሉት ናቸው። ያስታውሱ! የእናት ንብ መኖሯን ለማረጋገጥ አንደኛው ዘዴ በአካል እራሷን ማየት ሲሆን ይህ ካልሆነ በጥንቃቄ የእለት እንቁላል ወይም ለጋ እጭ መኖሩን በማየት የእናት ንብ መኖሯን ማረጋገጥ ይቻላል። 33 • ንቦች በሚዋለዱበት ወቅት ንግሥት (እናት) ንብ ብዙ እንቁላል ስለምትጥልና ስለሚፈለፈሉ የቦታ መጣበብ ሊከሰት ስለሚችል ለርብራብ ቀፎ ተጨማሪ ርብራብ ማስገባት ያስፈልጋል። • ለፍሬም ቀፎም ሰም መጋገርና ድራቢውን ቀፎ በማዘጋጀት መደረብ ያስፈልጋል። በዚህ ጊዜ በመሃል ንቡ ተዋልዶ እንዳይሄድ የውስጥ ቁጥጥር ማድረግ ተገቢ ነው። ያለን ኅብረ ንብ ብዛት እንዲጨምር የምንፈልግ ከሆነ ኅብረ ንቡ ከመዋለዱ በፊት በከፈላ ማባዛት ይቻላል (የዚህን ማኑዋል የእናት ንብ አረባብ ዘዴን ይመልከቱ)። ዓላማችን ማር ማምረት ከሆነ ደግሞ የተሠሩ የንግሥት ንብ አርኬናዎችን ቆርጦ ማስወገድና ድራቢ በመደረብ ተጨማሪ ቦታ መስጠት ነው። ከፍሬምና ከርብራብ ቀፎ ውስጥ የንግሥት ንብ ማገጃ የምናስገባ ከሆነ ከማር መቁረጫው ቀን ከ20 ቀናት ቀደም ብሎ ማስገባት ያስፈልጋል። ቀፎ መደረብ ቀፎ መደረብ ማለት ከመጀመሪያው እናት ቀፎ ላይ ተጨማሪ ቀፎ መጨመር ነው። በፍሬም ቀፎ ድራቢ የምንደርበው የውስጥ ቁጥጥር ስናካሂድ የቦታ ጥበት መኖሩን ከተገነዘብንና ንቡን ለኡደት የሚያበቁ ሁኔታዎች ካሉ ንቡ ተከፍሎ ከመሄዱ በፊት ንቦች ተጨማሪ ቦታ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው። ቀፎ መደረብ የሚያስፈልግ መሆኑን በሚከተሉት ሁኔታዎች ማረጋገጥ ይቻላል። • ንቦች በብዛት ከቀፎው ውጭ በዓይነ ብለጡ በኩል ወጥተው ሲታዩ፣ • ቀፎው ተከፍቶ በሚታይበት ጊዜ የቦታ መጣበብ መኖሩ ሲረጋገጥ፣ • ከአስሩ ፍሬሞች ውስጥ አብዛኛው በዕጭ ወይም በኮብኩባ ተሞልተው ሲገኙና፣ • ሠራተኛ ንቦች የእናት ንብ አርኬና (የንግሥት ቤት) ሠርተው ሲገኙ ነው። 1) የመጀመሪያ ቀፎ መደረብ በፍሬም ቀፎ ላይ የመጀመሪያ ድራቢ በሚከተለው ቅደም ተከተል መደረብ ይቻላል፣ • የሚደረበውን ቀፎ ማጽዳት፣ ማጠንና በአስሩም ፍሬሞች ላይ ሰም አትሞ ማያያዝ፣ • የንብ ንድፋት መከላከያ ሙሉ ትጥቅ፣ የጭስ ማጨሻ፣ የቀፎ መክፈቻ መሮ፣ ብሩሽ ማዘጋጀት። የቀፎ አደራረብ በሁለት ዓይነት ዘዴ ማካሄድ ይቻላል፣ 1) ከእናት ቀፎ ውስጥ ያደገ ዕጭ፣ ኩብኩባና የታሸገ ማር የያዙ ፍሬሞችን ወደ መጀመሪያው ድራቢ ማስገባትና ከእናት ቀፎ በወጡት ፍሬሞች ልክ ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞችን በመተካት የሚካሄድ አደራረብ ነው። ከላይ በተገለጸው ዘዴ ፍሬም በማለዋወጥ ቀፎ የሚደረበው በሚከተሉት ቅደም ተከተል ነው። 34 • አስር የታተመ ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞች የያዘውን ተደራቢ ቀፎ ንቦች ከሚገኙበት ቀፎ አጠገብ ማስቀመጥ፣ • ንብ በያዘው እናት ቀፎ ዓይነ ብልጥ በኩል ጭስ ማጨስ፣ ከዚያም ከአንድና ሁለት ደቂቃ በኋላ የቀፎውን ክዳን ቀስ ብሎ መክፈት፣ • 5 ወይም 6 ያደገ ዕጭ፣ ኩብኩባና የታሸገ ማር የያዙ ፍሬሞችን በጥንቃቄና በየተራ በማውጣት ንቦችን ወደነበሩበት ቀፎ በብሩሽ በመጥረግና በመመለስ በሚደረበው ቀፎ መሀል ላይ ማስቀመጥ፣ በምትካቸው ከሚደረበው ቀፎ 5 ወይም 6 ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞች ንብ በያዘው ቀፎ ውስጥ ማስገባት፣ • ተደራቢውን ቀፎ በነበረው ሳጥን ላይ አስተካክሎ በመደረብ ቀፎውን መክደን። 2) ሌላው ዘዴ ፍሬም ሳይለዋወጥ የሚከናወን ሲሆን አደራረቡም ንብ በያዘው እናት ቀፎ ዓይነ ብልጥ በኩል ጭስ ማጨስ፣ ከዚያም ከአንድና ሁለት ደቂቃ በኋላ የቀፎውን ክዳን ቀስ ብሎ መክፈት፣ አስሩ ፍሬሞች ላይ ሰም የተያያዘበትን አዲስ ድራቢ ቀፎ ከእናቱ ቀፎ በላይ አስተካክሎ ማስቀመጥና ቀፎውን መክደን። የመጀመሪያው ተደራቢ ማለትም ሁለተኛው ቀፎ ከተደረበ በኋላ የንቦች ቁጥር ለመጨመርና ሌላ ድራቢ የሚያስፈልግበት ሁኔታ እስከ ሚፈጠር እንደ አካባቢው ከ15-21 ቀናት ሊወስድ ይችላል። 2) የሁለተኛ ቀፎ መደረብ • ሁለተኛውን ድራቢ (ሦስተኛውን ቀፎ) ለመደረብ አስፈላጊ የሚሆነው አብዛኛው ፍሬሞች በእንቁላል፣ በዕጭ፣ በኩብኩባ፣ በማርና በጽጌ ብናኝ (ድኝ) ሲሞሉ፣ የንቦች መብዛትና የቀፎው መጥበብ ሲከሰት፣ በተጨማሪም ሠራተኛ ንቦች የእናት ንብ አርኬና ሠርተው ሲገኙ ነው። • ወቅቱ የተራዘመ የአበባ ወቅት የሚገኝበት አካባቢ ካልሆነ በስተቀር ሁለተኛውን ድራቢ መጨመር አስፈላጊ ላይሆን ስለሚችል በቅድሚያ በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል። • ሁለተኛውን ድራቢ በሚከተለው መንገድ መደረብ ይቻላል፣ • አስር የታተመ ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞች የያዘ ተደራቢ ቀፎ፣ የንብ ንድፋት መከላከያ ሙሉ ትጥቅ፣ የጭስ ማጨሻ፣ የቀፎ መክፈቻ መሮ፣ ብሩሽ፣ የእናት ንብ ማገጃ፣ ውሃ ከነመርጫው ማዘጋጀት፣ • ቀጥሎም ተደራቢ ቀፎውን ንብ በያዘው ቀፎ አጠገብ ማስቀመጥ፣ • ንብ በያዘው ቀፎ በዓይነ ብልጡ በኩል ጭስ ማጨስ፣ ከዚያም ከአንድና ሁለት ደቂቃ በኋላ የቀፎውን ክዳን ቀስ አድርጎ መክፈት፣ ንቦች በላይ በኩል እንዳይወጡ በጭስ መከላከል፣ • አንደኛውን ድራቢ (ሁለተኛውን ቀፎ) አንስቶ ከመጀመሪያው ቀፎ ጎን ክዳኑ ላይ ማስቀመጥ፣ • ከመጀመሪያው ቀፎ ውስጥ ማርና የታሸገ ዕጭ የያዘውን ፍሬም በማውጣት በሁለተኛው ድራቢ (በሦስተኛው ቀፎ) ውስጥ ማስቀመጥና በወጡት ፍሬሞች ምትክ የታተመ ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞች ማስገባት፣ • በዚህ አሰራር ሂደት እናት ንቧ ከሠራተኛ ንቦች ጋር ወይም ከዕጩ ጋር ወደ ሦስተኛው ቀፎ ማሳሰቢያ! ሠራተኛ ንቦች የእናት ንብ አርኬና ወይም ቁሩንብ ሠርተው ከሆነ ድራቢውን ቀፎ ከመደረቡ በፊት እናት ንብ መኖሯን በማረጋገጥ ቆርጦ ማሰወገድ 35 እንዳትገባ ጥንቃቄ ለማድረግ እንዲቻል በቅድሚያ ንቦችን ከዕጩ ላይ በብሩሽ ወደነበሩበት ቀፎ መመለስ ያስፈልጋል፣ • ከዚህ በኋላ በመጀመሪያው ቀፎ ላይ የእናት ንብ ማገጃውን አስተካክሎ ማስቀመጥ። • ሁለተኛውን ቀፎ መልሶ ቀደም ሲል በነበረበት ሁኔታ በመጀመሪያው ቀፎ ከንግሥት ንብ ማገጃው በላይ ደርቦ ማስቀመጥ፣ በዚህ በሁለተኛ ቀፎ ውስጥም ማርና የታሸገ ዕጭ የያዙትን ፍሬሞች መርጦ በማውጣትና በሦስተኛው ቀፎ ውስጥ በማስቀመጥ በምትካቸውም የታተመ ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞች ከሦስተኛው ቀፎ አውጥቶ ማስቀመጥ፣ • በዚህ ዓይነት የሦስተኛው ቀፎ ከአንደኛውና ከሁለተኛው ቀፎዎች በተወሰዱ አስር በማርና የታሸገ ዕጭ በያዙ ፍሬሞች ቢሞላ የሚመረጥ ሲሆን ካልተቻለ ግን በጎደሉት ፍሬሞች ልክ የታተመ ሰም የተያያዘባቸውን ፍሬሞች በዳርና በዳር በኩል በማስገባት እንዲሞላ ማድረግ፣ በሁለተኛው ቀፎ ላይ አስተካክሎ ማስቀመጥና መክደን ያስፈልጋል። በማር ወቅት የሚደረግ እንክብካቤ ማር የታታሪ ንቦች የሥራ ውጤትና አናቢው ማግኘት የሚገባው ማበረታቻ ሽልማት ነው። ስለዚህ ማር ከበሰለ በኋላ በተገቢው መንገድ ተቆርጦ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። የማር መቁረጫ ጊዜ እንደ አካባቢው ሁኔታ ይለያያል። በአገራችን ያሉ የአበባ ወቅቶች በዋነኛነት ከመስከረም እስከ ህዳር (ታህሳስ) እና ከግንቦት እስከ ሰኔ ያሉት ወቅቶች ናቸው። እነዚህ ሁለት ወቅቶች ከመኸርና ከበልግ ዝናብ በኋላ ከሚከሰተው የአበባ ወቅት ጋር የሚያያዙ እንደመሆኑ የበልግ ዝናብ በሌለባቸው አካባቢዎች ከግንቦት እስከ ሰኔ ባለው ወቅት የእፅዋት አበባ ብቃት ላይኖርና ማር ላይመረት ይችላል። ከዚህ ለየት ባለ ሁኔታ በአንዳንድ አካባቢዎች በየካቲት ወር ማር ሊመረት ይችላል። ንብ አናቢዎች ማር ከቀፎ የሚቆርጡበት ወይም የሚያመርቱበት ጊዜ መድረሱን ለማወቅ የሚረዷቸው የሚከተሉት ምልክቶች ናቸው። • ቀፎው ያለበት አካባቢ ማር ማር ይሸታል፣ • ብዛት ያላቸው ንቦች ሲወጡና ሲገቡ ይታያሉ፣ • ድንጉል (አውራ) ንቦች በቀፎው አካባቢ ሞተው ይገኛሉ፣ • ንቦች በጣም ብርቱ፣ ቁጡና ተናዳፊ ይሆናሉ፣ ንቦች ሰውንም ሆነ እንስሳትን ከቀፎው 20 ሜትር ርቀት ድረስ በመሄድ ይናደፋሉ፤ ብዙ ማር ባከማቹበት ወቅት የንቦች ዋነኛ ሥራ ጠላትን መከላከል ነው፤ ስለዚህ ወደቀፏቸው ላለማስቀረብ ይከላከላሉ፣ • በምሽት ጊዜ ንቦች ከቀፎው ውስጥ በመሆን ወደ ውጭ አየር እንዲወጣ ክንፋቸውን ያርገበግባሉ፤ በዚህ ድርጊታቸው በማሩ ውስጥ የሚገኘውን የውኃ መጠን ይቀንሳሉ። • ቀፎውን ከፍተን ከላይ ያሉትን ቶፕ ባሮች (ፍሬሞች) ጠርዝ ስናይ በነጭ ሰም ተያይዞና የማር እንጀራው በጣም የወፈረ ማለትም እስከ 2.5 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ይኖረዋል፤ የማሩ እንጀራ ቢያንስ ሶስት አራተኛ የሚሆነው በንቦች ሰም ተደፍኖ ወይም ታሽጎ ይታያል። ያስተውሉ!  የንግሥት ንብ ማገጃ ቀፎ ውስጥ የምናስገባው ከማር መቁረጫው ቀን ከ20 ቀናት ቀደም ብሎ መሆን አለበት። የንግሥት ንብ ማገጃ ማር ከተቆረጠ በኋላ መነሳት ይኖርበታል። 36 • ለማር መቁረጫ የሚያስፈልጉ እቃዎች (ቁሳቁሶች) የሚከተሉት ናቸው። • ሙሉ የማናቢያ ትጥቅ (ዓይነ ርግብ፣ ቱታ፣ ጓንት፣ ቦት ጫማ) • የጭስ ማጨሻ፣ ለጭስ የምንገለገልባቸው (ኬሚካል ያልነካው የቃጫ ጆንያ፣ ቆረቆንዳ፣ ገለባ፤ ጭድ) ፡ ማሩ ጭስ ጭስ እንዳይል የኩበት ጭስ መጠቀም የለብንም! • መሮ፣ ባትሪ፣ ቢላዋ • ከባህላዊ ቀፎ የሚቆረጠው የማር እንጀራ የሚቀመጥበት እቃ ከነክዳኑ • የማር ማጣሪያ ወይም መጭመቂያ • የሚቀየር ፍሬም የያዘ ሳጥን • የዓይነ በጎ መግለጫ ሹካ • የማር ማጣሪያ ወንፊት • የማር ማጣሪያ ጨርቅ • የተጣራ ማር መያዣ ቢዶኒ ወይም ባልዲ • የተጣራ ማር ለሽያጭ የሚታሸግበት እቃ ናቸው። ከባህላዊ ቀፎ ማር የመቁረጥና የማጣራት ዘዴ ከባህላዊ ቀፎ ማር ለመቁረጥ የሚስፈልጉ ቁሳቁሶች የንብ ንድፋት መከላከያ ሙሉ ትጥቅ፣ የጭስ ማጨሻ፣ ባትሪ፣ ቢላዋ፣ የማር እንጀራ የሚቀመጥበት እቃ ከነክዳኑ፣ ከተገኘ የማር መጭመቂያ (ሀኒ ፕሬሰር)፣ የተጣራ ማር መያዣ ባልዲ ወይም ቢዶኒ፣ የማር ማጣሪያ ወንፊት፣ የማር ማጣሪያ ጨርቅ ናቸው። ማር በሚቆረጥበት ጊዜ በተቻለ መጠን ብዙ ንቦች እንዳይሞቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ማር በሚቆረጥበት ጊዜ ወለላው ማር በቀፎው ውስጥ ከፈሰሰ ቁጫጭ ወደቀፎው እንዲገባ ሊስብ ስለሚችል በጥንቃቄ መቁረጥ ይገባል። በተጨማሪም ማር በሚቆረጥበት ጊዜ ለንቦች ምግብ የሚሆን ከሁለት እስከ ሶስት የማር እንጀራ የሚሆን ማር ሳይቆርጡ መተው ያስፈልጋል። ማር ስንቆርጥ የበሰለውን ማር፣ ያልበሰለውን ማርና እጭ አቀላቅለው የያዙትን የማር እንጀራዎች በተለያዩ እቃዎች እየለዩ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ከዚህ በኋላም የአበባ ዱቄት፣ እጭና ሙሽሬ የያዙትን የማር እንጀራዎች በመምረጥ መልሶ ቀፎው ውስጥ እንጨት በማስደገፍ ማስቀመጥና ቀፎውን አስተካክሎ መክደን ያስፈልጋል። የተቆረጠውን ማር ለማጣራት የማር መጭመቂያ መሣርያ የሚገኝ ከሆነ የበሰለውን ማር ብቻ በትኩሱ በአቡጀዲ ወይም በተመሳሳይ ንጹህ ጨርቅ አስሮ በመጭመቂያ መሣርያው ውስጥ አድርጎ መጭመቅ፣ ከመሣሪያው የሚወጣውን ወለላ ማር በማጣሪያ ወንፊትና ጨርቅ ማጣራትና በሚፈለገው መጠን ለሽያጭ በሚቀርበብበት ሁኔታ በማሸግ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ሆኖም ከባህላዊ ቀፎ የሚቆረጠውን ማር ለማጣራት የሚስችል መጭመቂያ መሣሪያ ካልተገኘ የተቆረጠውን ማር በትኩሱ ባልዲ ውስጥ አድርጎ በመፈትፈት ለ12 ሰዓት እንዲቆይ በማድረግ ሰፈፉ ከላይ ስለሚንሳፈፍ ወለላውን ማር ከሰፈፉ መለየት ይቻላል። 37 ከርብራብ ቀፎ ማር የመቁረጥና የማጣራት ዘዴ ከርብራብ ቀፎ ማር ለመቁረጥ የሚስፈልጉ ቁሳቁሶች የንብ ንድፋት መከላከያ ሙሉ ትጥቅ፣ የጭስ ማጨሻ፣ ባትሪ፣ መሮ፣ ቢላዋ፣ የማር እንጀራ የሚቀመጥበት እቃ ከነክዳኑ፣ ከተገኘ የማር መጭመቂያ፣ የተጣራ ማር መያዣ ባልዲ ወይም ቢዶኒ፣ የማር ማጣሪያ ወንፊት፣ የማር ማጣሪያ ጨርቅ ናቸው። ከላይ የተዘረዘሩት እቃዎች ከተመቻቹ በኋላ በሚከተለው አሰራር መሠረት ማር የመቁረጥና የማጣራት ሥራውን ማከናወን ይቻላል።  በቀፎው ዓይነ ብልጥ በኩል ጭስ ካጨሱ በኋላ የቀፎውን ክዳን መክፈት፣  ቶፕ ባሮችን በመሮ በማላቀቅ እያንዳንዱን ቶፕ ባር መመልከትና ለአሰራር እንዲያመች ካስፈለገ ባዶ ቶፕ ባሮችን ከቀፎው ማውጣትና ማስቀመጥ፣  የበሰለ ማር የያዘውን ቶፕ ባር እየመረጡ ማውጣትና ማሩ ሲቆረጥ ንቦች እንዳይወጡ ከላይ በኩል በጨርቅ መሸፈን፣  ማር ከያዘው ቶፕ ባር ውስጥ ከሥሩ በኩል ያልበሰለ የማር እንጀራ ያለውን ከዚያው ላይ በቢላዋ መቁረጥና ማሩን በመያዣ እቃ ማስቀመጥ፣ የበሰለ ማር ከያዘው ቶፕ ባር ደግሞ ማሩን ቆርጦ በሌላ የማር መያዣ በማስቀመጥ ቶፕ ባሩን ወደቀፎው ውስጥ መመለስ፣  በተመሳሳይ መልኩ ከሁሉም ቶፕ ባሮች ማር መቁረጥ፣ እጭና ጽጌ ብናኝ በተጨማሪ የተወሰነ ማር ለንቦች ቀለብ መተው፣  የተቆረጠውን ማር ለማጣራት የማር መጭመቂያ መሳሪያ የሚገኝ ከሆነ የበሰለውን ማር ብቻ በትኩሱ በዘርዛራ ልብስ በመጭመቂያ መሣሪያው ማጣራት፣ ከመሣሪያው የሚወጣውን ወለላ በማር ማጣሪያ ወንፊትና ጨርቅ ማጣራትና በሚፈለገው መጠን ለሽያጭ በሚቀርብበት ሁኔታ በማሸግ ማዘጋጀት፣  ከዚህም ሌላ ያልበሰለውን ማር (ተለይቶ የተቀመጠውን) ለምግብነት ማዋል ወይም ቶሎ መሸጥ ያስፈልጋል፣ ያልበሰለ ማር ብዙ ከቆየ ውኃ በብዛት ስላለው በቀላሉ ተብላልቶ ሊበላሽ ይችላል። ከፍሬም ቀፎ ማር የመቁረጥና የማጣራት ዘዴ ከፍሬም ቀፎ ማር ለመቁረጥ የማር መቁረጫ ጊዜ መድረሱን በማረጋገጥና ለማር መቁረጫና ማጣሪያ የተዘረዘሩትን ቁሳቁሶች በማዘጋጀት በሚከተለው ቅደም ተከተል መሰረት የማር ቆረጣውን ሥራ ማከናወን ይቻላል።  ከፍሬም ቀፎ ማር የሚቆረጠው ከአንደኛውና ከሁለተኛው ድራቢዎች ብቻ ሲሆን የመጀመሪያው ቀፎ ዕጭ የሚራባበት ክፍል በመሆኑ ማር መቆረጥ የለበትም፣  በቀፎው ዓይነ ብልጥ በኩል ጭስ ካጨሱ በኋላ የቀፎውን ክዳን መክፈት፣  ከላይኛው ድራቢ ንቦችን በጭስ እያሸሹና የበሰለ ማር የያዘውን ፍሬም እየለዩ ከቀፎው በማውጣት በባዶ ቀፎ ወይም በሳህን ላይ ማስቀመጥ፣  ቀጥሎም የላይኛውን ድራቢን አንስቶ ማስቀመጥና ከታችኛው ድራቢ ደግሞ ንቦችን በጭስ እያሸሹ የበሰለ ማር የያዘውን ፍሬም እየለዩ ከቀፎው በማውጣት በባዶ ቀፎ ወይም በሳህን ላይ በማስቀመጥ ንቦች እንዳይገቡበት መክደን፣  በዚህ ዓይነት ከሁለቱ ድራቢዎች ሃያዎችንም ፍሬሞች በመፈተሽ መጣራት የሚገባውን የበሰለ ማር ካወጡ በኋላ ቀፎዎችን ወደነበሩበት መልሶ ክዳኑን መክደን፣ 38  የተቆረጠውን ማር ከቀፎው እራቅ አድርጎ ወደ ማጣሪያው ቦታ መውሰድና የማሩን ዓይነበጎ በሁለቱም ጎን በሹካ መክፈት፣  የማር ማጣሪያው መሣሪያ መያዝ በሚችለው የፍሬም ብዛት መጠን የማር እንጀራውን ከነፍሬሙ በማር ማጣሪያው በማስገባትና የማጣሪያውን እጀታ በመያዝ ማሽከርከር፣ እንደገና ፍሬሞችን ማገላበጥና ማሽከርከር፣ በዚህን ጊዜ የማሩ ወለላ በማጣሪያ መሣሪያው ጎንና ጎን ላይ እየተረጨ ከታች ይጠራቀማል፣  በመቀጠልም የማር ማጣሪያውን ከፍ ባለ ጠረጴዛ መሰል ነገር ላይ በማስቀመጥ ከስር በኩል የማር ማውጫውን መክፈትና በማር ማጣሪያ ወንፊትና ጨርቅ ማሩ እየተጣራ በማር መያዣ ቢዶኒ እንዲጠራቀም ማድረግ፣  ከዚህ በኋላ ለመሸጥ በታሰበው መጠን እያሸጉ ለገበያ ማቅረብ ይቻላል፣ ይሁን እንጂ ለማር መያዣነት የምንጠቀምበት እቃ እርጥበት የማይስብ፣ የማይዝግና አየር የማያስገባ መሆን ይኖርበታል። በአያያዝ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን ማሩ በቀላሉ ሊበላሽ ይችላል፣  ከቀፎው ውስጥ ማር የያዘው ፍሬም ከወጣና ማሩ ከተጣራ በኋላ ቢቻል በአንድና ሁለት ሰዓት ውስጥ ካልሆነ ቢበዛ በአንድ ቀን ውስጥ ወለላው ማር የተጣራለትን ፍሬም ከነሰፈፉ መልሶ ከወጣበት ቀፎ ውስጥ ማስቀመጥ፣  በየጊዜው ማር ስናጣራ የሚሰባበሩ ወይም ያረጁ የማር ፍሬሞችን አዲስ በታተመ የሰም እንጀራ መተካት ያስፈልጋል። በድርቅ ወቅት ለኅብረ ንቦች የሚደረግ እንክብካቤ በተስማሚ የአበባ ወቅት በአንድ ቀፎ ውስጥ ከ40,000-60,000 የሚሆኑ ንቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የምግብ እጥረት በሚከሰትባቸው የበጋና የክረምት ወራት በአንድ ቀፎ ውስጥ የሚኖረው የንብ ብዛት ከ6,000-10,000 ድረስ እና በታች ሊሆን ይችላል። የምግብ እጥረት በሚኖርበት ጊዜ እናት ንቧ የምትጥለውን የእንቁላል መጠን ትቀንሳለች ወይም ታቋርጣለች፤ የተጣሉት እንቁላሎችም እጭ እንደሆኑ ሳይፈለፈሉ ሊሞቱ ይችላሉ። በክረምት ወራት ንቦች ከቀፏቸው ውስጥ ሲወጡ ዝናብ ከመታቸው ክንፋቸው ሊጣበቅ ስለሚችል ለመብረር ያስቸግራቸዋል። በክረምት ወራት አብዛኛዎቹ ዛፎች የማያብቡ ከመሆናቸውም በላይ የሚያብቡ ቢኖሩም የሚቀስሙት የአበባ ወለላ ማር በዝናብ ውኃ ስለሚሞላ እና ጽጌ ብናኙም ስለሚረጥብ ወይም በዝናብ ስለሚታጠብ መኖ ለመሰብሰብ አይችሉም ወይም ያስቸግራቸዋል። እንዲሁም በበጋ ወራት የማር አበባዎች ይደርቃሉ፣ የተወሰኑ አበባዎች ቢገኙም በቂ የአበባ ወለላ ማርና የጽጌ ብናኝ ላይኖራቸው ይችላል፤ ብዙዎቹ የውኃ አካላት ስለሚደርቁ የውኃ እጥረትም ሊያጋጥም ይችላል። በዚህን ጊዜ ለንቦች የተለዩ እንክብካቤዎችን ማድረግ ያስፈልጋል ኅብረ ንቦች ደካማ ሲሆኑ የደከሙ ኅብረ ንቦች ከሌሎች የሚለዩበት ውጫዊ ዳሰሳ በመጠቀም በዓይነ ብልጣቸው በኩል የሚታዩ የኅብረ-ንቡ ቁጥር አነስተኛ መሆን፤ የቀፏቸውን ዓይነ ብልጥ በሙጫ ማጥበብ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ የውስጥ ዳሰሳ በሚደረግበት ጊዜ ሊታይ የሚችለው ምልክት የማር እንጀራቸውን አለመሸፈን፤ የማር እንጀራው ደረቅነትና ባጠቃላይ የንቦች ቁጥር ማነስ ነው። በዚህን ጊዜ በተቻለ መጠን እናት ንብ መኖሯን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። እናት ንባቸው ካለችና የመኖ ችግር ካለባቸው ያልሸፈኑትን የማር እንጀራ በማውጣትና በመመገብ ለሚቀጥለው ወቅት ማድረስ ይቻላል። ሆኖም 39 እናት ንብ ከሌለችና ቀጣይ ወራቶች አበባ ላያገኙ ይችላሉ ብለን ምናስብ ከሆነ ወደ ተሻለው ቀፎ መደረብ (ማቀላቀል) የተሻለ አማራጭ ይሆናል። የፍሬም ቀፎ ድራቢ መቀነስ በድርቅ ወቅት የአበባ ዕፅዋቶች በማይኖሩበት ወቅት ለንቦች የሚሆን ተጨማሪ ምግብ በማዘጋጀት መመገብ ድራቢ ቀፎዎችን መቀነስና የእናት ንብ ማገጃ ማውጣት ያስፈልጋል። ድራቢውን ለማንሳት የሚያስፈልገው ጊዜ ለመደረብ የሚያስፈልገውን ያህል ላይወስድ ይችላል። ምክንያቱም ከላይ ከፍተን በምናይበት ጊዜ ንቦች ንግሥት ወደምትገኝበት ወደታችኛው መሠረት ቀፎ ስለሚወርዱ አስፈላጊ ከሆነ በሥርዓት ከከፈትን በኋላ መጠነኛ ጭስ ከላይ በማጨስ ንቦች ወደታች ሲሸሹ ድራቢውን ማንሳት ይቻላል። በሚቀነሰው ድራቢ ውስጥ የተሻለ ማር ያለው እንጀራ ካለ ከታችኛው ቀፎ ባዶ ፍሬም በማውጣት በመተካት ሥራውን ካጠናቀቅን በኋላ በጥንቃቄ ክዳኑን መክደን ያስፈልጋል። ከተቀነሰው ድራቢ ውስጥ ያለው ባዶ የማር እንጀራ በሰምበል ትል እንዳይጠቃ በንፁህ ጨርቅ ወይም ኬሻ ውስጥ አድረጎ በማሰር በደረቅና ቀዝቃዛ ቦታ ማስቀመጥ ተገቢ ነው። በዚህ ዓይነት በጥንቃቄ ከተቀመጠ ለሚቀጥለው ወቅት ልንጠቀምበት እንችላለን። ለንቦች ተጨማሪ መኖ መመገብ ንቦች እንደሌሎች የቤት እንስሳት እንድንመግባቸው የማይመርጡ ቢሆንም ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ልዩ ልዩ ምክንያቶች ለረሀብ አደጋ በሚጋለጡበት ጊዜ በሕይወት ለማቆየት የሚያስችላቸው ምግብ ልናቀርብላቸው ይገባል። ስለዚህ ንቦችን በድረቅ ወራት የውስጥ ቁጥጥር በማድረግ በቀፏቸው ውስጥ የማር እንጀራም ሆነ ድኝ እንደሌላቸው ከተረጋገጠ ለንቦች ተጨማሪ መኖ መመገብ ያስፈልጋል። በባህላዊ መንገድ ለንቦች ቀለብነት ከሚያገለግሉት መኖዎች ውስጥ ሽሮ ከትንሽ በርበሬ ጋር ቀይጦ በማቅረብ፣ ገብስ ወይም በቆሎ እንደበሶ አዘጋጅቶ በማቅረብ፣ የተወቀጠ ተልባና ኑግ በማቅረብ፣ የበሰለ ፓፓያና ማንጎ ሰንጥቆ በመስጠት፣ የቦሎቄ ዱቄት፣ የሸንኮራ አገዳ ጭማቂ፣ ወተት መሳሰሉትን በማቅረብ ከረሃብ ጉዳት ልናድናቸው እንችላለን። በዘመናዊ አሰራር ደግሞ ንጹህ ማር በንጹህ እቃ አድርጎ፣ ማር በዉኃ በጥብጦ፣ ሁለት እጅ ስኳር አንድ እጅ ውኃ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ከተበጠበጠ በኋላ በቀፏቸው ውስጥ በዕቃ በመጠቀም ንብ አናቢው ንቦችን ይመግባል። የዚህ አመጋገብ ዘዴ በተደጋጋሚ የሚካሄድ ሳይሆን ለአንድ ጊዜ መመገብ ይበቃል። ቀለባቸውም የሚቀርብላቸው በየቀፏቸው ውስጥ ቢሆን ይመረጣል። ከዚህ በተጨማሪ በድርቅ ወራት በተለይ ንጹህ ውኃ በየዕለቱ መቅረብ አለበት። ውኃ በድርቅና ሙቀት በሚበዛበት ሰዓት የዕለት ምግባቸውን ለማዘጋጃነት ከሚጠቀሙበት በተጨማሪ የቀፎውን ውስጣዊ ሙቀት ለመቆጣጠሪያ ስለሚጠቀሙበት ንጹህ ዉኃ በየቀኑ ማቅረብን መዘንጋት የለበትም። 40 ንቦችን ከቦታ ቦታ በማዛወር ማነብ በጓሮ አካባቢ የንብ ማነብን ሥራ ማካሄድ በአገራችን አርሶ አደሮች የተለመደ አሰራር ነው። ከዚህም ሌላ ንብ አናቢዎች በድርቅ ወቅት ቀፎዎችን በአንድ ቦታ አስቀምጦ ከመተው ይልቅ አበባ ወደሚገኝበት ቦታ በጥንቃቄ እያዘዋወሩ በማስቀመጥ ንቦች በቀላሉ የተለያዩ የማር እጽዋትን እንዲቀስሙ ቢያደርጉ የማር ምርታቸው ሊጨምር ይችላል። በተጨማሪም የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ሰብሎችንና እጽዋትን ንቦች በተቀመጡበት አካባቢ ማልማት ለንብ አመች ሁኔታን ስለሚፈጥር ጥሩ የማር ምርት ያስገኛል፤ የሰብል ምርቱም ይጨምራል። መሠረታዊ የንብ አያያዝ ጥንቃቄዎች የንብ ማናብ ተግባር ክህሎትን የሚጠይቅ የግብርና ሙያ ነው። ልምድ ያላቸው አናቢዎች ሥራውን በተገቢው መንገድ ሊያከናውኑት ይችላሉ። ሆኖም ነባሮችም ሆኑ ወደ ልማቱ የሚገቡ አዲስ አናቢዎች የሚከተሉትን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ ንቦችን ከማስቆጣትና አናቢዎችንም ከመነደፍ ያድናሉ። • ቀፎን ከፍቶ ልዩ ልዩ ተግባራትን ለማከናወን ተመራጭ የሚሆነው ጊዜ ማታና ንቦች ረጋ ባሉበት ጊዜ ነው፣ • ወደ ንብ ማናቢያ ጣቢያ ስንገባና ቀፎ ስንከፍት ከመነደፍ የሚከላከልልንን ሙሉ ትጥቅ መልበስ ይገባል፣ • ቀፎ ስንፈትሽም ሆነ ሌላ ሥራ ስንሠራ በንቦች መውጫና መግቢያ (በቀፎው ዓይነ ብልጥ) በኩል መቆም የለብንም፤ ምክንቱም ያልተለመደ አደናቃፊ ነገር ሲያገኙ ንቦች ይበሳጩና ይናደፋሉ፣ • ቀፎን ከፍተን ጭስ ስናጨስ በመጠኑና ለአጭር ጊዜ መሆን አለበት፤ በጣም የበዛ ጭስ ንቦችን ሊያበሳጫቸውና ተናዳፊ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ለንቦች የምንጠቀመው ጭስ ጠንካራ ጠረን የሌለው እንደ ቃጫ፣ ቆረቆንዳ፣ የገብስ / የስንዴ ገለባና ጭድ ያሉትን መጠቀም አለብን፣ • ቀፎን ከፍተን ስንሠራ በእርጋታና በጥንቃቄ መሆን አለበት፣ ቀፎውም እንዳይነቃነቅ መጠንቅ ያስፈልጋል፣ • ቀፎ ከፍተን ርብራቦችን / ፈሬሞችን ስንመልስና ክዳኑን ስንከድን በተቻለ መጠን ንቦች እንዳይጨፈለቁ መጠንቀቅ ይኖርብናል፤ ንቦችን ብንገድል ሌሎች ንቦች እንድኝደፉ የሚያነሳሳ ንጥረ ነገር ስለሚረጩ ጉዳት ሊደርስብን ይችላል፣ • አንደ ቱታ፣ ዓይነርግብ፣ ጓንት የመሳሰሉ የንድፋት መከላከያ ትጥቆችን ለሦስት ጊዜ ከተጠቀምንባቸው በኋላ ማጠብ ይኖርብናል፤ የንቦች መርዝ ሽታ እና ቆሻሻው ነገር ንቦችን ያስቆጣቸዋል፣ • ሽቶ ተቀብተን፣ ዲኦዳራንት ተጠቅመን፣ ሽታ ባላቸው ሳሙናዎች ታጥበን ወይም አልኮል ጥንቃቄ ንቦችን ከመቀለብ ይልቁን በምርት ወቅት ለኅብረ-ንቡ በቂ ማር መተው ይመረጣል። በተጨማሪም የስኳር ብጥብጥ ከቀፎ ውጭ ከመመገብ ይልቁን ከውስጥ መመገቡ ሊከሰት የሚችለውን የእርስ በእርስ ዝርፊያና እልቂት ያስወግዳል። ዝርፊያ ማለት የአንዱን ኅብረ-ንብ ማርና ድኝ የሌሎች ኅብረ-ንብ አባላት ቀምተው መውስድ ማለት ነው። በኅብረ ንቦች መካከል ዝርፊያ ከተነሳ በቀላሉ የሚቆም ስለማይሆን አስቀድሞ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። 41 ጠጥተን ወደ ንብ ማናቢያ ጣቢያዎች መቅረብ የለብንም፤ ምክንያቱም እንደነዚህ ዓይነት ሽታ ያላቸው ነገሮች ንቦችን ያስቆጣሉ፣ • የንብ ንድፋት መከላከያ ትጥቅ ሳንለብስ ንቦች ወደ እኛ በሚመጡበት ጊዜ እጆቻችንን በራሳችን ላይ እያወዛወዝን ከመሮጥ ይልቅ ጎንበስ ብሎና በእጅ ፊትን ሸፍኖ በዝግታ እርምጃ መሸሽ ይመረጣል፤ ምክንያቱም ፈጣን እንቅስቃሴ ንቦችን ይስባል፣ ያበሳጫቸዋል። ከንብ ማነብ ጋር የተለምዶ አባባሎች ንብ ማነብ በማህበረሰቡ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆየ የግብርና ንዑስ ዘርፍ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለምዶ የሚነገሩ ኋላቀር/ባህላዊ አባባሎች በሰፊው ይደመጣሉ። እነዚህ አባባሎች በሳይንስ ያልተደገፉ ሲሆኑ በዚህ ግብርና ዘርፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲያስከትሉ ቆይተዋል። ከንቦች እንክብካቤ ጋር የተያያዙ፣ ከሴቶች የንብ ማነብ ተሳትፎ ጋር የተዛመዱ አባባሎች በስፋት እንደየ ቦታው ሁኔታ ሲነገሩ ይስተዋላል። ለምሳሌ፡- 1) ወንዶች የግበረ-ሰጋ ግንኙነት ካደረጉ ወደ ንብ ጋጣ መጠጋት የለባቸውም፣ 2) ሴቶች በወር አባባ ወቅት ወደ ንቦች ቀፎ ከተጠጉ ንቦች ይሞታሉ፣ 3) በክረምት ሰዎች ወደ ንቦች ጋጣ መግባት/መጋት የለባቸውም ምክንያቱም ንቦችን መብረቅ ይመታቸዋል፣ 4) በአዲስ አመት ነጭ ዶሮ ማረድ ነጭ ማር ለማግኘት ይረዳል፣ 5) ነጭ ልብስ ተለብሶ ወደ ንቦች ጋጣ መጠጋት የለብንም፣ 6) ሴት ማር ማምረት የለባትም ምክንያቱም ምርት ይቀንሳል፣ 7) ባለ ፍሬም ቀፎ እንጀራ ያተላል፣ ከላይ የተዘረዘሩት አባባሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነገሩ እንጅ ምንም ዓይነት እውነታነት የሌላቸው ናቸው። ለምሳሌ ነጭ ማር የሚመረተው ንቦች ከሚቀስሙት የንቦች ቀሰም ዓይነት ብቻ እንጂ ከነጭ ዶሮ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። ባለ ፍሬም እንጀራ ሊተላ የሚችለው ማሩ ከተመረተ በኋላ ድራቢውን ቀፎ በመቀነስ ፋንታ ከነበረበት ላይ ይተውታል። በዚህን ጊዜ ሰምበልትል በንቦች ያልተሸፈነው እንጀራ ላይ እንቁላሏን በመጣል እንቁላሉ ይፈለፈላል። የተፈለፈለው ትል ድሩን በማድራትና ደረቅ እንጀራውን በመመገብ ድሩን እያደራ በእንጀራው ላይ ይታያል። በዚህን ጊዜ ንቦቹ እስከ መሰደድ ይደርሳሉ። ለዝርዝር ማብራሪያው የማኑዋሉ የንብ ጤናን ክፍልን ይመልከቱ። 42 ክፍል 4፡ የንብ ሥነ-ህይወትና ኅብረ ንቦችን ማባዛት 4.1. የንብ ሥነ-ሕይወት ማር የሚያመርቱ ንቦች በኅብረት የሚኖሩ እና ከእፅዋት አበቦች ምግባቸውን ሰብስበው የሚመገቡ በራሪ ነፍሳት ናቸው። ቁጥራቸው በዛ ያሉ በቀፎ ውስጥ እና ለኑሮ በሚስማማቸው ስፍራ በአንድነት የሚኖሩ ንቦች ኅብረ ንብ ይባላሉ። የኅብረ ንብ አባላት  አንድ ኀብረ ንብ ወይም የንብ ቤተሰብ የሚከተሉትን አባላት በውስጡ የያዘ ነው። እነዚህም ንግሥት (እናት) ንብ፣ ሠራተኛ ንቦችና አውራ ንቦች (ድንጉላዎች) በመባል ይታወቃሉ። በአንድ ቀፎ ውስጥ የሚኖሩ ንቦች በአንድ ላይ እስከ እንድ ኪሎ ድረስ ሊመዝኑ ይችላሉ። ንግሥት (እናት) ንብ  በጾታዋ ሴት ስትሆን የኅብረ ንብ እናት ነች፣  ከሌሎች ንቦች በሰውነቷ የገዘፈች ስትሆን አርሶ አደሮች በተለመዶ አውራ ንብ እያሉ ይጠሯታል፣  ደረቷ ጥቁርና ከሠራተኛ ንቦች ደረት የሚበልጥ ነው። የሆዷ ቀለም ቀላል ወይም ደማቅ ቡናማ ነው፣  የንግሥት ንብ የሆድ ክፍል (ሕልፅ) ወደ ጫፉ ቀጠን ብሎ ረዘም ያለ ስለሆነ ክንፎቿ ሙሉ በሙሉ አይሸፍኑትም፣  እግሮቿ ረጃጅምና ቡናማ ወይም ቀላ ያለ ቀለም አላቸው፣  ሌላ ንግሥት ንብ ብቻ የምታጠቃበት የመንደፊያ አካል (ጦር) አላት፣ 43  በተለየ ምክንያት ካልሞተች የሕይወት ዘመኗ እስከ አምስት ዓመት ይደርሳል፣  በአንድ ኅብረ ንብ ውስጥ አንድ እናት ንብ ብቻ ትገኛለች፣ ነገር ግን በኅብረ ንቦች መራቢያ ጊዜ አልፎ አልፎ ሁለትና ሦስት ንግሥት ንቦች ለአጭር ጊዜ አብረው ሊገኙ ይችላሉ፣ ሁለትና ከዚያ በላይ ንግስት ንቦች ካሉ የንግስት ንቦች የእርስ በርስ ንክሻ ሊፈጠር ይችላል። ሠራተኛ ንብ አውራ ንብ ንግሥት ንብ ምስል 10፡ የኅብረ ንብ አባላት ሠራተኛ ንቦች ሠራተኛ ንቦች በአንድ ቀፎ ውስጥ ከሚገኘው ኀብረ ንብ በጣም ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ ናቸው። ቁጥራቸው አበባ በማይገኝበት ወቅት ይቀንሳል። እነዚህ የቤተሰብ አባላት በጾታቸው ሴቶች ሲሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር እንቁላል አይጥሉም። የሠራተኛ ንቦች የሰውነት መገለጫ የሚከተለውን ይመስላል።  ሰውነታቸው ከአውራና ከንግሥት ንብ ያነሰ ነው፣  ሆዳቸው ከቀላል ቡናማ ቀለም እስከ ጠቆር ያለ ነጠብጣብ ሲኖራቸው አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሙሉ ጠቆር ያለ ይሆናል፣  እግሮቻቸው ጥቁር ሲሆኑ በተፈጥሮ የአበባዱቄትንና የተክሎችን ሙጫ ስለሚያሰባስቡ የኋላ እግሮቻቸው ሰፋፊና ጠንካሮች ናቸው፣  መንደፊያቸው ከሆዳቸው መጨረሻ ክፍል የሚወጣ ሲሆን ከተናደፉ በኋላ ትንሽ ቆይተው ይሞታሉ፣  እድሜያቸው ከ 42 ቀናት እስከ 4 ወራት ብቻ ነው። አውራ ንብ (ድንጉላ)  ይህ የህብረ ንብ አባል በጾታው ወንድ ነው፣  ትልቅና ወፍራም ሰውነት አለው፣  ሰውነቱ በትላልቅ ጸጉሮች የተሸፈነ ነው፣  መልኩ ጠቆር ያለ አንድ አይነት ቀለም አለው፣  በረራ ላይ እያለ የሚያሰማው ድምጽ ወፍራም ነው፣  መናደፍም ሆነ ራሱን መመገብ አይችልም፣ 44  ድንጉላ ንብ ሁልጊዜ እንደ ሌሎች የቤተሰብ አባላት በቀፎ ውስጥ የሚገኝ ሳይሆን ወቅቱን ጠብቆ እንዲራባ የሚደረግ ነው፤ በመሆኑም የድንጉላዎች ቁጥር ወቅትን መሠረት ያደረገ ነው። በጥሩ የአበባ ጊዜና በንቦች የመውለጃ ጊዜ እስከ ሺዎች የሚደርሱ አውራ ንቦች ይፈጠራሉ፣  በሕይወት የሚቆየው እስከ 2 ወር ብቻ ነው፤ ሆኖም የመኖ እጥረት በማይኖርበት ወቅት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ሊቆዩ ይችላሉ፣  ድንጉላ ከሌሎች የህብረ ንብ አባላት በሚከተሉት ባሕሪያት ይለያል፣  ሰውነቱ ወፍራም እና ሞላ ያለ ሲሆን ጡንቻው በጣም የዳበረ ነው፤ ይህም በበረራ ላይ እናት ንብን ለማጥቃት እንዲችል ይረዳዋል፣  ዓይኖቹ ከሌሎች ቤተሰብ አባላት በበለጠ ትላልቅ ሲሆኑ ይህም እናት ንብን በሩቅ በቀላሉ እንዲያያት ያስችለዋል፣  የስራ ድርሻው ከንግስት ንብ ጋር ግንኙነት ማድረግ ብቻ ነው። የንቦች እድገት ደረጃዎች የንቦች የእድገት ደረጃ የሚጀምረው ንግሥት ንብ ከምትጥለው እንቁላል ነው። የንቦች የእድገት ደረጃ አራት ክፍሎችን የያዘ ነው። እነዚህም፡-  እንቁላል (ያልታሸገ ዓይነ-በጎ)  እጭ (ያልታሸገ ዓይነ-በጎ)  ሙሽሬ (የታሸገ ዓይነ-በጎ) እና  ሙሉ እድገት (ጉልምስ ንብ) ናቸው ምስል 11 የንቦች ሙሉ ዑደት (የእድገት ደረጃ) ንግሥት ንብ በአውራ ንቦች ከተጠቃች በኋላ ሁለት ዓይነት እንቁላሎች ትጥላለች። ከንግሥት ንብ የእንቁላል ማኩረቻ ክፍሎች እንቁላሉ ሲጣል ወደ ዓይነ በጎው በሚወስደው ቱቦ አንድ በአንድ በሚሄድበት ጊዜ ከስፐርማቲካ ውስጥ የሚወጣ ከወንድ አባለዘር ጋር ከተገናኘ የለማ (የዳበረ) እንቁላል ሆኖ ይጣላል ማለት ነው። ይህ የለማ እንቁላል ሠራተኛ ንቦች ወይም ንግሥት ንብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከእንቁላሎች ውስጥ የተወሰነው ተፈጥሮአዊ በሆነ ሁኔታ ከአባላዘር 45 ሳይገናኝ ስለሚጣል ድንጉላ ንብ ሆኖ ይፈለፈላል። ድንጉላ ንብ በእናቱ በኩል ወንድ አያት እንጂ አባት የለውም። አንድ ንግሥት ንብ ብዙ አበባ ባለበት ወቅት በየቀኑ እስከ 2000 እንቁላሎችን መጣል ትችላለች። ንግሥት ንብ እንቁላሎችን የምትጥለው በሠራተኛ ንቦች ተሰርቶ በተዘጋጀላት የሰም እንጀራ ላይ በእያንዳንዱ ዓይነ በጎ (እንቁራ) ላይ በማስቀመጥ ሲሆን እንቁላሎቹ በተጣሉ በሶስተኛው ቀናቸው ወደ እጭነት ይፈለፈላሉ። እጩ በጣም ትልቅ የሆነ የምግብ መምጠጫ አካል ያለው ሲሆን በሠራተኛ ንቦች ለስድስት ቀናት ያህል እየተመገበ ከቆየ በኋላ በሰባተኛው ቀን ክፍት የነበረው ዓይነ በጎ ይደፈንና ወደ ኩብኩባ የእድገት ደረጃ ይሸጋገራል። ኩብኩባው ልዩ ልዩ የንብ አካላት ያለው ሲሆን መልኩ በመጀመሪያ ነጭ ይሆንና ለመፈልፈል ሲቃረብ ደግሞ ወደ ቡናማ መልክ ይለወጣል። ኩብኩባው ሲፈለፈል ወደ ሙሉ የእድገት ደረጃ ላይ የሚደርስ ሲሆን እንደተፈለፈለ ሠራተኛ የሆነው ንብ ግራጫ መልክ ይኖረዋል። የንብ አፈጣጠር በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ ከላይ የተመለከተውን ቢመስልም ሠራተኛ ንቦች፤ ንግሥት ንብና አውራ ንቦች ከእንቁላል እስከ ሙሉ እድገት ደረጃ ለመድረስ የሚወስድባቸው ጊዜ ግን ይለያያል (ሠንጠረዥ 3 ይመልከቱ)። ስለሆነም ንግሥት ንብ በ16 ቀን ትፈለፈላለች፣ ሠራተኛ ንቦች እንቁላሉ ከተጣለበት ጀምሮ 21 ቀን ሲሞላቸው ሲፈለፈሉ አውራ ንቦች ግን ዘግይተው በ24 ቀናቸው ይፈለፈላሉ። ሠንጠረዥ 3፡ የንቦች የእድገት ደረጃና የሚፈጁት ቀናት ብዛት የእድገት ደረጃ ንግሥት ሠራተኛ ድንጉላ የእንቁላል ጊዜ 3 3 3 የእጭና የመመገቢያ ጊዜ 4-5 5-7 8 የሙሽሬ (የእሽግ) ጊዜ 7-8 10-11 12 ጠቅላላ የሚወስደው ጊዜ 14-16 18-21 23-24 እንደተፈለፈሉ ያላቸው ከብደት (ሚ.ግ) 200 100 200 ርዝመት (ሚ.ሜ) 18 - 22 12 - 15 15 - 17 46 ምስል 12፡ እናት ንብ የጣለችውን እንቁላል የቀፎ ውስጥ የሠራተኛ ንቦች ሲንከባከቡት የኅብረ ንብ አባላት የሥራ ድርሻ በአንድ የንብ ቤተሰብ ውስጥ የሚገኙ አባላት የተለያየ የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን ዝርዝር ተግባራቸውም የሚከተለው ነው። የንግሥት ንብ ተግባር እናት ንብ ከተፈለፈለች በኋላ በጥቂት ቀናት ውስጥ በአውራ (ድንጉላ) ንብ ትጠቃለች። ከድንጉላ ንብ ጋር ግንኙነት የምታደርገው በሕይወት ዘመኗ አንዴ ብቻ ነው። ሆኖም በአንድ ጊዜ ከ8 እስከ 10 ከሚሆኑ አውራ ንቦች ጋር ግንኙነት ስለምታደርግ በህይወት ዘመኗ ሊያገለግላት የሚችለውን የተባዕት አባለዘር በልዩ መያዣ (ስፐርማቲካ) ውስጥ ታከማቻለች። እናት ንብ በአውራ ንቦች ከተጠቃች በኋላ ከሦስተኛው ቀን ጀምሮ በጥሩ የአበባ ወቅት ከ1500 እስከ 2000 እንቁላሎች በቀን መጣል የምትችል ስትሆን ይህ በአንድ ቀን ብቻ የምትጥለው የእንቁላል ክብደት ከሰውነት ክብደቷ ይበልጣል፤ የምርታማነት ዘመኗም እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ነው። እናት ንብ የምታመነጨው ንጥረ ነገር ሠራተኛ ንቦችን የሚማርክ ሽታ ያለው ስለሆነ በዚሁ ምክንያት ኅብረ ንቡን በአንድ ቤተሰብ መልክ እንዲኖር በማድረግና ሁሉም የቤተሰብ አባላት የሚጠበቅባቸውን የሥራ ድርሻ እንዲወጡ ታደርጋለች። 47 የሠራተኛ ንቦች ተግባር ሠራተኛ ንቦች በኅብረ ንቡ ውስጥ ወሳኝ አባላት ናቸው፤ የተለያዩ የቀፎ ውስጥና ከቀፎ ውጭ ያሉትን ሥራዎች ያከናውናሉ። ስማቸው እንደሚያመለክተው እነዚህ የህብረ ንብ አባላት ሁሉንም ሥራ የሚያከናውኑትና ሥራውንም የሚወስኑት እነርሱ ናቸው። ተግባሮቻቸውም እንደየ እድሜያቸው የተለያዩ ሲሆን ዋና ዋና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፡-  እናት ንብን ከእራሳቸው በሚገኝ እጢ በመጠቀም የንብ ወተት ማመንጨትና መመገብ እንዲሁም መንከባከብ፣  ከሆዳቸው በሚገኝ ስምንት የሰም ማመንጫ እጢዎች በመጠቀም ሰምን ማመንጨትና ርቀቱን በመጠበቅ የማር እንጀራ መገንባት፣  ከራሳቸው እጢ የንብ ወተት (ሮያል ጀሊ) በማመንጨት እጮችንና ንግሥት ንብን መመገብ፣  ድንጉላ ንብና እጭን መመገብና መንከባከብ፣ የእጭን የዕድገት ደረጃ በመጠበቅ በስስ ሰምና ፕሮፖሊስ ዓይነበጎውን ማሸግ፣  የቀፎን የውስጥ ክፍል ማጽዳት፣  ፈሳሽ የአበባ ወለላን የእርጥበት መጠኑን በመቀነስና በማስተካከል ማር መሥራት፤ የእርጥበት መጠኑ የተስተካከለውን የማር ዓይነበጎ በስስ ሰም ማሽግ፣  የቀፎ ውስጥ ሙቀት መቆጣጠር፣  ቀፎን ከጠላት መከላከል፣  ፈሳሽ የአበባ ወለላ (ቀሰም)፤ የአበባ ዱቄት፤ የንብ ሙጫና ውኃ መሰብሰብ የመሳሰሉትን ያከናውናሉ። ከፍተኛውን የቤተሰብ ሥራ ለመሥራት ያበቋቸው በሚከተሉት የሰውነት ተፈጥሯቸው በመጠቀም ነው።  የአፋቸው ክፍል (መቅሰሚያቸው) ከሌሎች የረዘመ ሲሆን ይህም በቀላሉ ቀሰም እንዲሰበስቡ ይረዳቸዋል፣  የኋላ እግሮቻቸው ጠንካሮችና ከረጢት መሳይ አካል አላቸው፤ ይህም የአበባ ዱቄትና ሙጫ (ማረገና) ለመሰብሰቢያ ይረዳቸዋል። ምስል 13፡ ሠራተኛ ንቦች ከሌሎች የንብ ቤተሰቦች ልዩ የሚያደርጋቸው አካላት ሠራተኛ ንቦች ምግብ ለማምጣት ከቀፎ ወጥተው ሲሄዱ በሰዓት እስከ 24 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ይበራሉ። ሆኖም የአበባ ወለላ፣ ጽጌ ብናኝ፣ ውሃና ሙጫ ይዘው ወደ ቀፎአቸው ሲመለሱ በሰዓት የሚበሩበት ፍጥነት እስከ 20 ኪሎ ሜትር ነው። ንቦች ለመብረር ኃይል ሰጭ ምግብ (ካርቦሃይድሬት) ያስፈልጋቸዋል። በዚህ መሰረትም አንድ ሠራተኛ ንብ ለ15 ደቂቃዎች በረራ ከ20-40 ሚሊግራም ኃይል ሰጭ ምግብ ያስፈልጋታል። 48 የድንጉላ ንቦች ተግባር የድንጉል ንብ ብቸኛ ተግባሩ የተፈለፈለች ድንግል እናት ንብ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም ሲሆን ከግንኙነት በኋላ ብልቱ ስለሚቆረጥ ወዲያውኑ ይሞታል፤ በቀፎ ውስጥ የቀሩትም ቢሆኑ የመኖ እጥረት በሚኖርበት ጊዜና ቦታ ሲጠባቸው በሠራተኛ ንቦች ተጎትተው ይጣላሉ ወይም ይገደላሉ። የንቦች ማህበራዊ አኗኗር የንቦች ማህበራዊ አደረጃጀት ህብረ ንቡ ህልውና እና ውጤታማነት ወሳኝ ነው። እያንዳንዱ ዓይነት ንብ ለቀፎው አጠቃላይ ተግባር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ልዩ ሚናዎች እና ኃላፊነቶች አሏቸው። በንቦቹ መካከል ያለው ቅንጅት እና ትብብር ምግብን በብቃት እንዲሰበስቡ፣ ዘር እንዲተኩ እና ቀፎውን እንዲጠብቁ ያስችላቸዋል። ንቦች በማህበራዊ ከሚኖሩ ጥቃቅን ነፍሳት ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፤ በኅብረት ስለሚኖሩም የንብ ቤተሰብ አባላት የተለያየ የሥራ ድርሻ አላቸው፣ • የእናት ንብ በምታመነጨው ልዩ የተፈጥሮ ጠረን የተነሳ አንድ ኅብረ ንብ የራሱን ቀፎ ጠረን ለይቶ ይኖራል፤ስለሆነም የግላቸው የሆነ የቀፎ ጠረን ስላላቸው ወደ ሌላ ቀፎ አይገቡም፣ ወደ ቀፏቸውም ሌላ ንቦችንም አያስገቡም ነገር ግን ቀሰም ከያዙ ከሌላም ቀፎ የመጡ ንቦችንም ቢሆን ያስገቧቸዋል፣ • የጋራ የሆነ ተልዕኮንም ለማሳካት የሚንቀሳቀሰው ከዚህ ከእናት ንብ ልዩ ጠረን (መዓዛ) ላይ ተመሥርቶ በሚተላለፍ ትዕዛዝ ነው፣ • በዚህም የተነሳ በአንድ ቀፎ ውስጥ የሚገኝ ቁጥሩ ከ40,000 እስከ 60,000 የሚደርስ ኅብረ ንብ በአንድ ትዕዛዝ ለአንድ የጋራ ግብ በተቀናጀ መልኩ ተግባብቶ በኅብረት ይሠራል፣ • ስለሆነም ጣፋጭ የሆነውን ወርቃማ ማርና ሌሎችንም ጠቃሚ ምርቶች ይሠራሉ። ዋና ዋና የንብ ባሕርያት የንቦች ባሕሪ በምንልበት ጊዜ ንቦች በተናጥልም ሆነ በጋራ የሚያሳዩት ወይም የሚያደርጉት ድርጊት ማለት ነው። የንብ ባሕሪያት ቀድሞ ማወቅ ከንቦች ጋር አብሮ ለመሥራት ያስችላል። የሠራተኛ ንቦች መግባቢያ ንቦች የተለያዩ ስራዎችን የሚያከናውኑ ሲሆን የእርስ በርስ ግንኙነታቸውም ከሰው ልጅ ቀጥሎ ሙሉ መልዕክትን በቀላሉ መለዋወጥ የሚችሉ ነፍሳት ናቸው። በዚህም መሰረት የሚፈልጉትን መልዕክት ለሌሎች ንቦች የሚያስተላልፉበት ሶስት ዓይነት የመግባቢያ ዘዴዎች አሏቸው። • ከሰውነታቸው በሚመነጩ ንጥረ ነገሮች፣ • በሰውነት እንቅስቃሴዎቻቸው (በሆዳቸው ዳንስ በመደነስ ወይም በመርገብገብ) • በድምፅ • በመነካካትና የያዙትን ምግብ ለሌሎች በማቅመስ ነው። 49 የንበ ባሕሪያት ከምንላቸው ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው። • የማር እንጀራቸውን ከላይ ጀምረው ወደታች ይሠራሉ፣ ከታችና ከጎን የማር እንጀራውን ማገናኘት ያልተለመደ ነው፣ • ከአንዱ የማር እንጀራ እስከ ጎን ከሚገኘው የማር እንጀራ ያለው እርቀት ሁል ጊዜ እኩል ነው፣ ይህም የንቦች መተላለፊያ ቦታ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቢ ስፔስ ይባላል፣ • ንቦች ለምግብነት በቂ የሆነ ጽጌ ብናኝና ፈሳሽ የአበባ ወለላ ያስፈልጋቸዋል፣ • ንቦች መነሻ ቦታቸውን (ቀፎአቸውን) መሰረት አድርገው ይንቀሳቀሳሉ፣ • ንቦች በቀፎ ውስጥ በቀላሉ የሚግባቡበት ቋንቋ አላቸው፣ • ንቦች በአንድ ጊዜ አንድ የቀሰም ዓይነት ብቻ ይቀስማሉ፤ ለምሳሌ አንድ ንብ በኑግ አበባ ቀሰም ብትጀምር በዚያው ጉዞዋ ከሌላ አበባ ቀሰም አትሰበስብም፣ • ሠራተኛ ንቦች ቦታ ሲጠባቸው፣ እናት ንብ ስታረጅ ወይም በአደጋ ምክንያት ስትሞት የተጣለውን እንቁላል በመንከባከብና ብዙ የንብ ወተት በመመገብ ወደ ንግሥት ንብ ያሳድጉታል፤ ከዚህ በኋላ ንቡ ስለሚወልድ ተከፍሎ ሊሄዴ ይችላል፣ • የንቦች የቁጡነት ወይም የገራምነት ባሕሪ በተለያዩ ሁኔታዎች ይወሰናል፣ የንቡ ዝርያ፣ የአካባቢው የአየር ጸባይ፣ የአናቢው የአያያዝ ሁኔታና የመሳሰሉት የንቦችን ቁጡነት ወይም ገራምነት ይወስናሉ፣ • ንቦች የመኖሪያ አካበቢው ካልተስማማቸውና በተደጋጋሚ ሲረበሹ የነበሩበትን ቀፎ ለቀው ይሰደዳሉ። 4.2. ኅብረ ንብ የማባዛት ዘዴ አንድ የንብ ንግሥት በአማካኝ በቀን ከ1500 እስከ 2000 ምቹ ሁኔታ ካጋጠማትም እስከ 3000 እንቁላል ልትጥል ትችላለች። በመሆኑም እናት ንብ ለንብ እርባታው ብዛት ያለው ንብ እንዲኖርና ጥሩ የማር ምርት እንዲመረት ለማድረግ ያላት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ሠራተኛ ንቦች ቀፎ ሲጠባቸው፣ እናት ንብ ስታረጅባቸው ወይም ስትሞትባቸው ሌላ እናት ንብ ተክተው እንደሚያሳድጉ እና እንደሚዋለዱ ወይም ተከፍለው እንደሚሄዱ ይታወቃል። ከዚህም በተጨማሪ በሰው ሠራሽ ዘዴ እናት ንቦችን በማስፈልፈል ኀብረ ንቦች እንዲባዙ ማድረግ የሚቻል ሲሆን ይህም የሚከተሉት ጠቃሜታዎች አሉት። • በቀፎው ውስጥ የምትገኝ ያረጀች እናት ንብን ለመተካት፣ • በተለያየ ምክንያቶች የሞተች ወይም የጠፋች እናት ንብን ለመተካት፣ • የኀብረ ንብ ዝርያን ለማሻሻል እና፣ • የኀብረ ንብ ቁጥርን ለማብዛት • የንቦች ዝርያ ለማሻሻል ማለትም በምርታማነትና በተፈላጊ ባህርይ የሚመረጡትን ንቦች በማዳቀል ለማባዛት፣ • ንቦችን በማባዛትና በመሸጥ ገቢ መጠንና አይነት ለማሳደግ • ንቦች ተከፍለው እንዳይሄዱ ለመከላከል • ለዘር ማዳቀል ሥራ ለማዘጋጀት ናቸው። 50 የሚባዛው ኀብረ ንብ የሚመረጥበት ዘዴ ለመክፈል ወይም ለማባዛት የሚመረጠው ኀብረ ንብ የማርና የንብ ውጤቶችን አዋጭ በሆነ መንገድ ለማምረት የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት አለበት፤ • ጠንካራና ብዛት ያለው፣ • ምርታማ የሆነ፣ • ወደ ርብራብ ወይም የፍሬም ቀፎ ከተዛወረ ከ1 ዓመት በላይ የሆነው፣ • በጥሩ ፀባዮቹ የታወቀ ሊሆን ይገባል። ኀብረ ንብ የሚባዛበት ጊዜ ኀብረ ንብ የሚባዛበት ጊዜ የአካባቢው ኀብረ ንብ ወልዶ የሚወጣበት ወይም በባህላዊ እውቀት ንብ አናቢ ገበሬዎች ኀብረ ንባቸው ወልዶ ወጥቶ እንዳይሄድባቸው መከላከል የሚጀምሩበት ወቅት ነው። ጊዜው በየዓመቱ እንደየአካባቢው የአበባ ብዛትና የኀብረ ንቡ ጥንካሬ ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ሊቆይ ይችላል። በአጠቃላይ ንግሥት ንብ የማባዛት ወይም የማራባት ሥራ መከናወን ያለበት አብዛኛዎቹ የቀሰም አበባዎች ማበብ በሚጀምሩበት ወቅት ቢሆን ይመረጣል። ምክንያቱም በዚህ ወቅት በሚከፈለው ቀፎ ውስጥ ብዛት ያለው ሠራተኛ ንብ፣ ማር እና ድኝ፣ እንቁላል፣ ለጋ እጭ፣ ያደገ እጭ ሊገኝ ስለሚችል ነው። ከዚህ ሌላ በዚህ ወቅት በቂ ድንጉላዎች ስለሚፈጠሩ እናት ንብ ከተፈለፈለች በኋላ በድንጉላ እንድትጠቃ ያስችላታል። ኀብረ ንብን ለማባዛት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና የማናቢያ ቁሳቁሶች • የሚከፈለው ኀብረ ንብ • የመክፈያ ቀፎ • የንብ ንድፋት መከላከያ ሙሉ ትጥቅ • ጭስ ማጨሻ • ባትሪ ወይም መብራት • የማር መቁረጫ ቢላዋ • ቃጫ ወይም ግራንጣ • ሰሌን (ሸራ ምንጣፍ) የማባዣ ቀፎ ጠቅላላ ይዘቱ ለማር ምርት የምንጠቀምበትን የርብራብ ቀፎ ወይም የፍሬም ቀፎ ዓይነት ሆኖ እርዝመቱን ብቻ በመቀነስ ይዘጋጃል። አንድ ለማባዣ የምንጠቀምበት ቀፎ 10 ርብራቦች ወይም 5 ፍሬሞችን ለመደርደር የሚበቃ ሆኖ ይሠራል። ይህም የተከፈሉት ኀብረ ንቦች እራሳቸውን በማላመድ በቀላሉ ንግሥታቸውን እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል። ከቀፎው ላይ የምንጠቀምበት ርብራብ ወይም ፍሬም ከትልቁ የርብራብ ወይም ፍሬም ቀፎ ከምንጠቀምበት ጋር በስፋቱ እኩል ስለሆነ በሚቀጥለው የአበባ ወቅት ንቡ ሲዳብር ወደ ትልቁ ቀፎ በቀላሉ ለማዛወር ይረዳል። 51 ምስል 14፡ የማባዣ ቀፎዎች (ግራ፡ የርብራብ ቀፎ ማባዣ፤ ቀኝ፡ ፍሬም ቀፎ ማባዣ) ኅብረ ንብ የሚባዛባቸው ዘዴዎች ኅብረ ንቦችን በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ዘዴዎች ማባዛት ይቻላል። በተፈጥሮ ንግሥት ንብ የማባዛት ዘዴ ኅብረ ንቦች በተፈጥሮ እየተራቡ ትውልዳቸው እንዲቀጥል ያደርጋሉ። ይህንን የንቦች ባሕሪ በመረዳት የአገራችን አናቢ አርሶ አደሮች ባላቸው ልምድ ኅብረ ንቦችን ያባዛሉ። በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ እውቀቱ ያላቸው ንብ አናቢዎች ኅብረ ንቦችን በጠባብ ቀፎ ወይም በቅል በማድረግ ተከፍሎ የሚወጣውን ኅብረ ንብ በመያዝ ወደ አዲስ ቀፎ በማስገባት የኅብረ ንባቸውን ቁጥር ይጨምራሉ። ከዚህም ሌላ በፍሬም ቀፎ የተዛወረን ኅብረ ንብ ተጨማሪ ቦታ (ድራቢ) በወቅቱ የማንደርብለት ከሆነ ሊወልድ ይችላል። አዲስ ኅብረ ንብ ተወልዶ የሚወጣው በሞቃታማ ቀን ጠዋት አራት ሰዓት አካባቢ ሲሆን ወደ አዲሱ ስፍራ የሚወስዱት ቃኝ (አሳሽ) ንቦች ከመመለሳቸው በፊት በቀፎው አቅራቢያ በሚገኝ ዛፍ ወይም አጥር ላይ ይሰፍራል። አሳሽ ንቦች ለቅኝት ከሄዱበት ቦታ ከመመለሳቸው በፊት ይህን ሰፍሮ ከሚገኝ ኅብረ ንብ ውስጥ ንግሥት ንቧን በጥንቃቄ ይዞ በቁፍጣን (queen cage) ውስጥ በማድረግ በሌላ በተዘጋጀ ቀፎ ውስጥ ማስቀመጥ ይቻላል። ምስል 15፡ ንቦች በከፊል ተከፍለው ዛፍ ላይ ሲያርፉ 52 በተፈጥሮ የሚዋለድ ኅብረ ንብ ከሦስት እና ከዚያ በላይ በተከታታይ ሊወልድ ይችላል። በዚህን ጊዜ አናቢዎች ተወልዶ የሚወጣውን ንብ በመያዝ በጠባብ ቀፎዎች ያስቀምጣሉ። ተወልዶ የሰፈረ ኅብረ ንብን በመያዝ የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛ ውልድ መሆኑን ማወቅ ይቻላል። በመጀመሪያ የተወለደ ኀብር ንብ ከሆነ (Prime swarm) • ብዛት ያለው የመስክ ሠራተኛ ንቦችን እና ነባር ንግሥት የያዘ ስለሆነ ንግሥት ንብ ወዲያውኑ እንቁላል መጣል ትጀምራለች፣ • ከ3 ሳምንት በኋላ አዲስ ሠራተኛ ንቦችን ማግኘት ይቻላል፣ • ኀብረ ንቡ ቶሎ ያድጋል፣ በፍጥነት ይደረጃል ሁለተኛ ጊዜ የተወለደ ከሆነ (After swarm) • ይህ ቀፎ ድንግል ንግሥት ንብ የያዘ ስለሆነ መጀመሪያ መጠቃት ይኖርባታል፣ • ከተጠቃች ከአራት ቀናት በኋላ ንግሥት ንብ እንቁላል መጣል ትጀምራለች፣ • በመሆኑም ኅብረ ንቡ ቀስ በቀስ እየተጠናከረ ይሄዳል። ከሁለተኛው ውልድ በኋላ የሚወለዱት ኅብረ ንቦች ድንግል ንግሥት ንብ እና ወጣት ሠራተኛ ንቦችን የያዙ ናቸው። እነዚህ ኅብረ ንቦች በቁጥራቸው ጥቂት ስለሚሆኑ በአዲስ ቀፎ ውስጥ ብናስቀምጣቸው ላይለምዱ ይችላሉ። በተለይም ወጣት ሠራተኛ ንቦች ከመስክ ቀሰም መሰብሰብ ስለማይችሉ በርሃብ ተመናምነው ሊያልቁ ይችላሉ። ስለዚህ የሚከተሉትን አማራጮች ማድረግ ተገቢ ነው። • ከሰፈሩበት ቦታ ላይ እናት ንብ ፈልጎ በመያዝ ወደ ተዘጋጀ ቀፎ ውስጥ ማስቀመጥ፣ ለማጠናከርም ከሌላ ቀፎ ውስጥ ከ2-3 የማር እንጀራ ከቀፎዉ አውጥቶ መስጠት፣ • በዚህ መልኩ ተጨማሪ እናት ንብ ከተፈጠረ በንብ ማናቢያ ጋጣ ውስጥ በምርታማነታቸው ደካማ የሆኑ ኅብረ ንቦች ካሉ የእነሱን እናት ንብ በማውጣትና በመግደል መተካት ይቻላል። በሰው ሠራሽ ዘዴ ንግሥት ንብ የማባዛት ዘዴዎች የምንፈልገውን ብዛት ያህል ንግስቶች ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ተፈልፍለው የሚወጡበት ቀናት በውል ስለማይታወቅ ተፈልፍለው በመውጣት ሊጠፉ ስለሚችሉ እና ሁሌም ስለማይወለዱ ንግስቶች በፈለግን ጊዜ ሁሉ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ የሚሉት የተፈጥሮ መራቢያ መንገዶች ደካማ ጎኖች ተደርገው ይወሰዳሉ። ስለሆነም ሰው ሰራሽ የንግስት ማርባት ዘዴዎች መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በአሁኑ ጊዜ ያለውን የኀብረ ንብ እጥረት ለመቅረፍ እና ዘመናዊ አሰራርን ለማምጣት በተለያዩ ሰው ሠራሽ ዘዴዎች ኀብረ ንብን ማባዛት ይቻላል። ይህ ዘዴ በንብ አናቢው አማካኝነት ሠራተኛ ንቦችን ንግሥት ንቦች እንዲፈጥሩ በማነሳሳት የሚከናወን ተግባር ነዉ። በተለያዩ የሰው ሠራሽ 53 ዘዴዎች ንግሥት ንብን ማባዛት ይቻላል። ከነዚህም ዘዴዎች ውስጥ በምርምር ተሞክሮ ውጤታማ የሆነ እና በአርሶ አደሩ በቀላሉ ሊሰራ የሚችል ኀብረ ንብ የማባዛት ዘዴ ንቡን በመክፈል እና ሚለር በሚባል ዘዴ ብዙ ንግሥት ንቦችን በማባዛት ነው። ኅብረ ንብ ከፈላ በከፈላ ኀብረ ንብ የማባዛት ዘዴ በርብራብ እና በፍሬም ቀፎ የሚገኝ አንድን ጠንካራ ኀብረ ንብ ከሁለት እስከ አራት በመክፈል የኀብረ ንብ የሚባዛበት ዘዴ ነው። ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት በባህላዊ ቀፎ የሚገኝን ጠንካራ እና ብዛት ያለው ኀብረ ንብ ወደ ርብራብ ወይም የፍሬም ቀፎዎች በሚሸጋገርበት ወቅት ከባህላዊ ቀፎ ውስጥ የሚገኘውን ንብ እና የማር እንጀራ እኩል በማካፈል ወደ ሁለት ቀፎዎች በማስገባት ከፈላ በማካሄድ ማሸጋገር እንደሚቻል በተግባር ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል። ኀብረ ንብ የሚከፈልበት ቅደም ተከተል ኀብረ ንብ የሚከፈልበት ቅደም ተከተል እንደሚከተለው ነው። • የሚከፈለውን ኀብረ ንብ ስኳር ወይም ማር በውኃ በወፍራሙ በጥብጦ ለ2-3 ቀናት በመመገብ ማጠናከር፣ • ከፈላው ከሚካሄድበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ የሚከፈለውን ኀብረ ንብ የውስጥ ፍተሻ በማድረግ የሚከተሉትን ነጥቦች ማየት ወይም ማረጋገጥ ያስፈልጋል። o የንቡን ጥንካሬ፣ o እናት ንብ መኖርዋን፣ o እንቁላል፣ ያላደገ እጭ፣ ማር፣ ድኝ፣ መኖሩን፣ o ንቡ ጤናማ መሆኑንና፣ o የተፈጠረ የእናት ንብ አርኬና (Queen Cell) መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። • የንብረት ቆጠራ በማድረግ በዚህን ጊዜ በእያንዳንዱ ርብራብ ወይም ፍሬም ላይ እንደ አቀማመጣቸው ቅደም ተከተል መሰረት ምልክት ወይም ቁጥር በመስጠት ርብራቡ ወይም ፍሬሙ የያዘውን ነገር ማለትም እንቁላል፣ ለጋ እጭ፣ የተሸፈነ እጭ፣ ባዶ የማር እንጀራ፣ ማርና ድኝ፣ በማለት ምዝገባ ማካሄድ፣ • በሚቀጥለው (ከፈላው በሚካሄድበት) ቀን ማታ ከላይ በቁጥር 2.3 የተጠቀሱት የማናቢያ ቁሳቁሶች በማሟላት ከፈላውን ማካሄድ፣ • የውስጥ ኅብረ ንብ ፍተሻ በማካሄድ ካገኘነው መረጃ በመነሳት ከፈላውን ትክክለኛ የእናት ንብ መፈጠሪያ አርኪና ካገኘን እናት ንብ ከዚሁ አርኪና ልትፈጠር እንደምትችል ግንዛቤ በመያዝ ከፈላውን ማካሄድ ይቻላል። እንዲሁም ሠራተኛ ንቦች እንቁላል ወይም ለጋ እጭ ካገኙ አሳድገው ንግሥት ንብ እንድትፈለፈል ያደርጋሉ፣ • እናት ንብ በተቻለ መጠን ከመጀመሪያው ቀፎ ውስጥ እንድትቀር ማድረግ ያስፈልጋል፤ ከፈላው በሚካሄድበት ጊዜ እናት ንብን መያዝም ሆነ ከየትኛው ክፋይ ቀፎ መኖሯን ማረጋገጥ አድካሚ በመሆኑ፤ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ከምንከፍላቸው ቀፎዎች ሁሉ ተመሳሳይ የሀብት ክፍፍል ማድረጋችንን እርግጠኛ መሆን ነው፣ • እናት ንብን ፈልገን መያዝ ከቻልን ወይም ከየትኛው ቀፎ ውስጥ መኖሯን ካረጋገጥን እናት ንብ ከሌለችበት ቀፎ ውስጥ ለአዲሷ እናት ንብ መፈጠሪያ አመች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል፣ 54 • ከፈላው ሲካሄድ ከሁሉም የተከፈሉ ቀፎዎች ውስጥ በቂ ንቦች መግባታቸውን ማረጋገጥ እና እያንዳንዱ የማር እንጀራ በንቦች መያዙን (መሸፈኑን) ማረጋገጥ ያስፈልጋል፣ • ከፈላው ከተካሄደ በኋላ ተከፍለው ሌላ ቀፎ ውስጥ የገቡት ንቦች እንዳይመለሱ ከተቻለ አንዱን ክፋይ ንብ ከነበረበት ላይ በመተው ሌላውን ክፋይ ንብ ከ300-400 ሜትር በላይ አራርቆ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ከሁለት እና ሶስት ሳምንት በኋላ ክፋዩን ንብ ወደ መኖሪያ ቦታው መመለስ እና ማስቀመጥ ይቻላል፣ • ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች አንዱን ቀፎ ራቅ ወዳለ ቦታ መውሰድ ካልተቻለ ዋናውን ቀፎ የንቦችን መውጫ እና መግቢያ በር (አይነ ብልጥ) አቅጣጫ በማዞር ከቦታው በማንሳት ሌላ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እና ዋናው ቀፎ ተቀምጦበት ከነበረው ቦታ ላይ ደግሞ የተከፈለውን ቀፎ በማስቀመጥ የመስክ ንቦች ቀፎአቸው ስለሚመስላቸው እየገቡ ክፋዩን ንብ ያጠናክሩታል፣ • የንብ ከፈላው ከተደረገበት ከሁለተኛ ቀን ጀምሮ የንቦችን የመውጣት እና የመግባት ሁኔታ እንዲሁም ቀሰም እና የአበባ ዱቄት ይዘው መግባታቸውን መከታተል ያስፈልጋል፣ • በሶስተኛው ቀን የውስጥ ቁጥጥር በማካሄድ ንቦችን የሚከናውኑትን ሥራ መመልከት፣ በተለየም፡- o የእናት ንብ ያለበት ቀፎ ከሆነ ተጨማሪ የእናት ንብ አርኬና ማሳደግ የለበትም፣ o የእናት ንብ የሌለበት ቀፎ ከሆነ ግን ሠራተኛ ንቦች የእናት ንብ አርኬና ማሳደግ ይጀምራሉ (ምስል 15: ይመልከቱ) ምስል 16: በማደግ ላይ የሚገኝ የእናት ንብ አርኬናዎች (ግራ) ፣ ለመፈልፈል የደረሰ እና እናት ንብ ተፈልፍላ የወጣችበት የእናት ንብ አርኬና (ቀኝ) • ከፈላው ከተደረገ ከ8ኛው እስከ 11ኛው ባሉት ቀናት የውስጥ ቁጥጥር በማካሄድ የተገነቡት የእናት ንብ አርኬናዎች መታሸጋቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። በዚህን ጊዜ የተስተካከለ ቅርጽ ያላቸው እና ከማር እንጀራው የታችኛው ጠርዝ በኩል ከሁለት እስከ ሶስት የሚሆኑትን አርኬናዎች መርጦ ከነመጠባበቂያው መተው እና ሌሎችን ቆርጦ ማስወገድ ወይም ለሌላ ንግሥት ለሌለው ኅብረ ንብ መስጠት ይቻላል፣ • ከ15ኛው እስከ 16ኛው ባለው ቀን እናት ንብ ትፈለፈለላለች። ይህንንም ለማወቅ በምልክት የተውነው የንግሥት ንብ አርኬና በምስል 15 እንደሚታየው ተከፍቶ ሊታይ ይችላል፣ ይህን ምልክት እንደታየ ሌሎች ያልተፈለፈሉ የእናት ንብ አርኬናዎችም ጊዜያቸውን እየጠበቁ ሊፈለፈሉ ስለሚችሉ እና ይህም ኅብረ ንቡ ተከፍሎ ሊወጣ ስለሚችል ማስወገድ ወይም ቆርጦ ለሌላ ኅብረ ንብ መስጠት ያስፈልጋል፣ • የቀሰም አበባ የሚኖርበት ትክክለኛው ወቅት እና ፀሃያማ ቀን ከሆነ እናት ንብ በተፈለፈለች ከ5ኛው እስከ 8ኛው ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ በድንጉላ (አውራ) ንቦች በአየር ላይ ትጠቃለች፣ 55 ምስል 17፡ የእናት ንብ እና የድንንጉል ንብ ግንኙነት፤ ድንጉላው ከግንኙነት በኋላ ብልቱ በእናት ንብ ብልት ላይ ተቆርጦ ስለሚቀር ወዲያውኑ ይሞታል አንድ እናት ንብ ተፈልፍላ ሰውነቷ ከዳበረ እና ከድንጉላ ንቦች ጋር ግንኙነት ለመፈጸም ብቁ ከሆነች በኋላ ከቀፎው ወጥታ በአየር ላይ ከመሬት 10-40 ሜትር ከፍታ እና ከ30-200 ሜትር ዙሪያ ውስጥ በመብረር አውራ ንቦችን የሚስብ ልዩ መዓዛ ታመነጫለች። በዚህ ጊዜም በማዕዛዋ የተማረኩ እና ብዛታቸው እስከ 200 ሊደርስ የሚችል አውራ ንቦች ይከተሏታል። ከላይ በተገለጸው ሁኔታ እናት ንብ ከስምንት እስከ አስር በሚደርሱ አውራ ንቦች ከተጠቃች በኋላ ሲበቃት ወደ ቀፎዋ ስትመለስ የመጨረሻውን የአውራ ንብ ብልት ቁራጭ ሠራተኛ ንቦች ነቅለው ይጥሉላትና በቀፎዋ ውስጥ ትቀመጣለች፣ ከዚህ በኋላ በህይወት ዘመኗ ለሌላ ግንኙነት ከቀፎዋ ተመልሳ አትወጣም። አንድ አውራ ንብ በሚያጠቃበት ጊዜ ወደ ሁለት መቶ ሚሊየን የሚሆን አባለዘር ያወጣል። ንግሥት ንብ ይህንን ከአውራ ንቦች ያገኘችውን አባለዘር እስፐርማቲካ በሚባል የአባለዘር ማከማቻ ከረጢቷ ውስጥ ታስቀምጠዋለች። ንግሥት ንብ ከተጠቃች ከሶስተኛው ቀን ጀምሮ እንቁላል መጣል ትጀምራለች። ለተባዛ ኅብረ ንብ የሚደረጉ ተግባራት ኅብረ ንብ ከተከፈለ ወይም ከተባዛ እና እናት ንብ ከተፈለፈለች በኋላ የውጫዊ እና ውስጣዊ ቁጥጥር (ፍተሻ) በማካሄድ ንቦች ለሚያጋጥማቸው ችግሮች አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል። የተከፈለው ወይም የተባዛው ኅብረ ንብ ጠንካራ ከሆነ፣ አካባቢው ከተስማማው እና እናት ንብ እንቁላል መጣል ከጀመረች የተከፈሉት ንቦች ከሁለት ወራቶች ጀምሮ የመክፈያ ቀፎአቸውን ከሞሉት እና ውጭ ማደር ሲጀምሩ ወደ ትልቅ (standard) የርብራብ ቀፎ ወይም የፍሬም ቀፎ ማዛወር ያስፈልጋል። አናቢው ለንቦችማስቀመጫ በቂ ቦታ ከሌለው እና እርባታውን ማስፋፋት ካልፈለገ የተከፈለውን ኅብረ ንብ በመክፈያ ቀፎ ውስት እንዳሉ መሸጥ ይችላል። የተከፈለው ኅብረ ንብ ለምዶ የተሻለ ምርት እንዲሰጥ ለንቦች የተሻሻለ አያያዝ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም መሠረት፡- • ንቦችን ከፀሀይ ከዝናብ እና ከብርድ የሚከላከከል ጋጣ መሥራት • ኅብረ ንቡ የተቀመጠበትን ቦታ ጽዳት መጠበቅ • በንቦች እና በምርታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱትን የንብ ጠላቶች መቆጣጠር 56 • ለንቦች የመኖ ምንጭነት ከሚያገለግሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ደኖች በተጨማሪ ለሰው ምግብነት፤ ለእንሰሳት መኖነት፤ ንቦች የሚቀስሟቸውን ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞችን የሚሰጡ ዕጽዋትን ማልማት፣ • በማር ቆረጣ ወቅት ለንቦች የተወሰነ ማር ማስቀረት፣ • በድርቅ ጊዜ ለንቦች ተጨማሪ መኖ እና ውኃ መስጠት እና • አስፈላጊ መረጃዎችን በየጊዜው መያዝ ያስፈልጋል። ሌሎች ቀላል የእናት ንብ እርባታ ዘዴዎች  ሚለር (raising queen in a zigzag cut comb)  ሆፕኪንስ (raising queens placed flat comb)  አሌይ (queen cells are raised on a prepared strip of cells)  ማጨናነቅ ወይም ማጣበብ (congestion)  እናት ንብን በማስወገድ (Raising queens in queen less colony)  በመክፈያ ቀፎ መቀነስ (Starting Queen Cells in a Nucleus)  መርጦ ማሳደግና ለንግስት አልባ መስጠት (Raising Queen on Whole Brood Comb)  ድርብርብ የዕጭ ቤት በማዘጋጀት (Raising Queens in Double Brood Hive) ዘመናዊ የእናት ንብ እርባታ ዘዴዎች 1. ግራፍቲንግ (Grafting) 2. ጀንተር (Jenter) 3. ሰው ሰራሽ የማዳቀል ዘዴ (Artificial Insemination) 57 ክፍል 5፡ የንብ ውጤቶች አመራረት፣ ማቀነባበርና ግብይት 5.1. የንብ ዉጤቶች ማምረት፣ ማቀነባበር እና ግብይት የንብ ውጤቶች የምንላቸው ማር፣ ሰም፣ የንብ ሙጫ (ፕሮፖሊስ)፣ ድኝ (ፖለን)፣ የንብ ወተት (ሮያል ጄሊ)፣ የንብ ዳቦ፣ የንብ መርዝ፣ ዕጭ የመሳሰሉት ሲሆኑ በተለያየ መንገድ ለመድሃኒትነት፣ ለምግብነት፣ ለኮስሞቲክስ እና ሌሎችም ግብዓት ይውላሉ። ከዚህ በታች ዋና ዋና የሚባሉትን የንብ ውጤቶች ጥቅም፣ የንጥረ ነገር ይዘታቸው፣ የአመራረት ሂደት፣ በምርትና ከምርት ሂደት በኋላ የአያያዝ ዘዴዎች ላይ እንደሚከተለው ማብራሪያ ቀርቧል። 5.1.1 የማር ምንነት፣ ጥቅም፣ ማምረት፣ ማቀነባበር እና ግብይት ማር ከንብ ውጤቶች በመጠንም ሆነ በሚያስገኘው ገቢ የመጀመሪያው እና ግንባር ቀደም ምርት ነው። ማር ከጥንት ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለ ምርት ነው። የሰው ልጅ ታሪክ የጀመረበት ዘመን እና ማር ጥቅም ላይ የዋለበት ዘመን ጎን ለጎን ይሄዳሉ። ማር በዓለም ላይ ያሉ ህዝቦች በተለያዩ የባህል መገለጫ ስርዓት ውስጥ ጉልህ ሚና ሲጫወት የኖረ ሲሆን ለምግብነት፣ ለተለያዩ እምነቶች እና ለመድኃኒት ሲያገለግል ኖሯል። ማር ያልተብላላ በጣም ጣፋጭ እና ንቦች ከአበባ ፈሳሽ ወለላ ክፍል በመሰብሰብ ወደ ትናንሽ የተፈጥሮ የስኳር መጠኖች (ፍርክቶስ፤ጉሉኮስ የመሳሰሉትን ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን) በመቀየር ንቦች የሚያዘጋጁት ተፈጥሮአዊ ምግብ ነው። ንቦች ከተለያዩ የማር እፅዋት ክፍል ፈሳሽ የሆነዉን የአበባ ወለላ በመቅሰም ወደ ቀፏቸው በመውሰድ እና የማር እንቆራ ውስጥ በማጠራቀም በውስጡ የሚገኘውን ውኃ (እርጥበት) እንዲተን እና መጠኑ እንዲቀንስ በማድረግ ያዘጋጁታል። ማር በዋነኛነት በዉስጡ የተፈጥሮ ስኳር እና ዉኃ የያዘ ሲሆን ከ78 በመቶ በላይ የሚሆነው ይዘት ስኳር ነው። ይህ የተፈጥሮ ስኳር በዋነኛነት ፍሩክቶስ፤ጉሉኮስ እና ሱክሮስ ይዟል። እነዚህ የስኳር አይነቶች ለማሩ መጣፈጥ፣ለኃይል ሰጪነት፣ ከአየር እርጥበት ለመሳብ እና ለሌሎች ባህሪያት እንዲኖረው አስተዋጽኦ አላቸው። 58 ማር በውስጡ የተለያዩ ለሰውነት ጠቃሚ የሆኑ ከ180 በላይ ንጥረ ነገሮችን ይዟል። ከነዚህም ንጥረ ነገሮች ዋና ዋናዎቹ ካርቦሀይድሬት፣ውሃ፣ማዕድን፣ፕሮቲን፣ኢንዛይም እና አሲድ ናቸው። ንጥረ ነገሮቹ ከየትኛውም አካባቢ በሚመረቱ የማር አይነቶች ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም መጠናቸው ሊለያይ ይችላል። ልዩነቱ የሚከሰተው በአብዛኛው ማሩን ለመስራት ንቦቹ የሚቀስሙት ፈሳሽ የአበባ ወለላ አመንጪ እፅዋት ዓይነት ስለሚለያይ፣ እነዚህ እፅዋት የበቀሉበት የአፈር አይነት እና የአየር ንብረትም አስተጽኦ ያደርጋል። የማር ጥራት በዉስጡ በሚይዘዉ ንጥረ ነገር፣ የዉኃ መጠን፣ በቀለም እና በጣዕም የሚለካ ሲሆን በዋነኛነት በማር ውስጥ የሚገኘው የውሀ መጠን ለማር የጥራት ደረጃ መለኪያ ወሳኝ መስፈርት ነው። በማር ዉስጥ የሚገኘዉ ውሀ ንቦች ቀስመው ከሚያመጡት የአበባ ወለላ የሚገኘ እና ወለላውን ወደ ማርነት ለመለወጥ በሚያደርጉት ጥረት የሚፈጠር ዉጤት ነው። ወለላው በንቦች ሲቀሰም በውስጡ የሚገኘው የውሃ መጠን ከ60-90 በመቶ ሲሆን፣ ወደ ቀፎው ከገባ በኋላ በቀናት ብዛት ንቦቹ ውሃውን በማትነን ከ18-29 በመቶ ዝቅ ያደርጉታል። በዓለም ገበያ ለገበታ የሚቀርበው ማር ውስጥ መገኘት የሚገባው የውሃ መጠን በአማካኝ ከ18-21 በመቶ ነው። የውሃው መጠን ከዚህ በላይ ከሆነ ማሩ ለፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃነት እንዲውል ይደረጋል። አብዛኛው የአገራችን ማር ያለው የውሃ መጠን የዓለም ዓቀፍ የጥራት ደረጃን ያሟላል። በማር ውስጥ የውሃ መጠን ከበዛ ማሩ ስለሚብላላ ቶሎ ይበላሻል፣ ይቆመጥጣል፣ቀለሙ እና ጣዕሙም ይቀየራል። በሀገራችን ለማር የዉሃ መጠን መብዛት ዋናዉ ምክንያት አናቢዎች በአብዛኛዉ ያልታሸገ (ያልበሰለ) የማር እንጀራ ስለሚቆርጡ ነዉ። ነገርግን ከግማሽ በላይ (ከ75 በመቶ በላይ) የተሸፈነዉን የማር እንጀራ ማምረት ከተቻለ የዉሃዉ መጠን በሚፈለገዉ የጥራት ደረጃ ማድረስ ይችላል። በማር ዉስጥ ከ20 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የስኳር ዓይነቶች የሚገኙ ሲሆን ግልኮስ እና ፍርክቶስ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። ማር በውስጡ አሲድ የያዘ ሲሆን አሲዱም ማሩ በተለያዩ ረቂቅ ተህዋሲያን እንዳይበላሽ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ነገር ግን የአሲድ መጠኑ ከፍ ካለ ማሩን ሊያቆመጥጠው ይችላል። በማር ውስጥ በብዛት የሚገኙ ማዕድናት ሶዲየም፣ ፓቲሲየም፣ ብረት፣ መዳብ፣ ክሎሪን እና ፎስፈረስ ናቸው። ማሩ እነዚህን ማዕድናት የሚያገኘው የማር እፅዋት ከሚበቅልባቸው የአፈር አይነቶች ነው። በተጨማሪም በማር ውስጥ ከሚገኙ ንጥረ ነገሮች ዉስጥ ኢንዛይም አንዱ ሲሆን የዚህ ንጥረ ነገር መኖር ማር ከሌሎች ጣፋጭ ነገሮች እንዲለይ አድርጎታል። እነዚህ ኢንዛይሞች ኢንቨርቴዝ እና ዲያሰቴዝ የሚባሉ ሲሆን ከንቦች የዉስጥ የሰዉነት ክፍል የሚመነጩ ናቸው። ንቦች የአበባ ወለላዉን ከቀሰሙ በኋላ ኢንዛይሞችን ከማሩ ጋር በመቀላቀል ከፍተኛዉን የሱክሮስ መጠን ወደ ጉሉኮስ እና ፍሩክቶሰ እንዲቀየር ያደርጉታል። ማር በአጠቃላይ በዉስጡ በሚይዛቸዉ ንጥረ ነገሮች በሁለት ይከፈላሉ፡- 1. 99 እጅ የሚሆነዉ ማር በዉስጡ ጉሉኮስ፤ ፍሩክቶስ፤ ሱክሮስ፤ ዉሃና ሌሎች ስኳር የያዘ ሲሆን 59 2. ቀሪዉ 1 እጅ ደግሞ አሲድ፤ ሚኒራል፤ ኢንዛይም፣ ፕሮቲን የያዘ ሲሆን እነዚህ ንጥረ ነገሮች የማሩን ቃና እና ጣዕም ከመወሰን አንፃር እጅግ ጠቃሚ ሲሆኑ በተጨማሪም የማር ጥራትን ለመለካት አስፈላጊ ናቸዉ። የማር ባህርያት ማር በርካታ ንጥረ ነገሮች በዉስጡ የያዘ በመሆኑ የተለያዩ ባህሪያት እንዲኖሩት ያደርገዋል። ዋነኞቹ የማር ባህሪያት ከአካባቢው አየር እርጥበት እና ሽታን የመሳብ፣ የመርጋት፣ የመዝለግለግ፣ የመቅለም እና የማጣበቅ፣የመቅለጫ የሙቀት መጠን፣ የእፍጋት መጠን ናቸው። እነዚህን ባህሪያት በአግባቡ በመረዳት እና መደረግ ያለባቸዉን ጥንቃቄ በማድረግ የማር ጥራትን ጠብቆ ለገበያ ተወዳዳሪ ማድረግ ተገቢ ነዉ። 1. መዝለግለግ ትኩስ የተቆረጠ ማር በጣም ዝልግልግ ፈሳሽ ነው። ትኩስ ማር በሚጣራበት ጊዜ ከእቃ ጋር ተጣብቆ በመቅረት የመባከን መጠኑ በጣም ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም ማርን በጥራትም ሆነ በመጠን ሳይባክን የሚጣራበት እና የሚታሸግበት ወቅት ከቀፎ ማሩ እንደተቆረጠ እና ትኩስ እንደሆነ መሆን አለበት። የማር መዝለግለግ ባህሪ በዋነኝነት በማር ውስጥ በሚገኙ ንጥረ ነገሮች የሚወሰን ቢሆንም በተለይ በማር ውስጥ የሚገኘው የተፈጥሮ ውሃ መጠን ወሳኝ ነው። የማር መዝለግለግ ባህሪን በሚገባ ጠንቅቆ በማወቅ የማር ብክነት በጥራትም ሆነ በመጠን እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል። በተለይ ማር በሚሰበሰብበት፣ በሚጣራበት፣ ፓምፕ በሚደረግበት፣ በሚረጋበት፣ በሚቀላቀልበት እና በሚታሸግበት ጊዜ የማር ብክነት እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል። ማርን በምናቀነባብርበት ወቅት የማር የመዝለግለግ ባህሪ ዝቅተኛ ከሆነማሩ በሚያልፍባቸው የማቀነባበሪያ እቃዎች ተጣብቆ በመቅረት ለብዙ ብክነት ይዳረጋል። እንዲሁም ከማሩ ጋር የተቀላቀሉ ትናንሽ ባዕድ ነገሮች ከማሩ ጋር ተጣብቀዉ በመቅረት የማሩን ጥራት ይቀንሳሉ። የማር የሙቀት መጠንን በመጨመር የማር የመዝለግለግ ባህሪን በመቀነስና እና እየተጣበቀ የሚቀረዉን እንዲቀንስ በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ማር ማግኘት ይቻላል። ትኩስ የተቆረጠ ማር የዉስጡ የሙቀት መጠን 35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነዉ። የማር መዝለግለግ ባህሪ በማር ውስጥ ባለው የውሃ መጠን ይወሰናል (ሠንጠረዥ 4)። ሰንጠረዥ 4፡ በማር ዉስጥ ያለዉ የዉሃ መጠን ሲቀንስ የማር የመዝለግለግ ባህሪ ሲጨምር የሚያሳይ ተ. ቁ የውኃ መጠን (%) የመዝለግለግ መጠን 1 13.7 420 2 15.5 138 3 18.2 48 4 20.2 20 60 ከሠንጠረዡ መረዳት እንደሚቻለው የማር የዉኃ መጠን ሲጨምር የማር መዝለግለግ ወይም ፈሳሽ መሆን ባህሪ ይጨምራል። እንዲሁም የማር የዉኃ መጠን ሲቀንስ የማር የመዝለግለግ ባህሪ ይቀንሳል። የማር የመዝለግለግ ባህሪ ከዉኃ መጠን በተጨማሪ በማር የዉስጥ የሙቀት መጠን ጋር ወሳኝ የሆነ ግንኙነት አለዉ። የማር የሙቀት መጠን ሲጨምር የማር የመዝለግለግ ወይም ፈሳሽ የመሆን ባህሪ ይጨምራል። የማርን የመዝለግለግ ባህሪ በአግባቡ ማወቅ ማርን እየተጣበቀ ብክነት ሳያደርስ በሚፈለገዉ ሁኔታ አቀነባብሮ ወደ ገበያ ለማቅረብ እና ውጤታማ ለማድረግ ይጠቅማል። የሚከተለው ሠንጠረዥ የማር የሙቀት መጠን ሲጨምር የማር የመዝለግለግና ማጣበቅ ባህሪው እንደሚቀንስ ያሳያል (ሠንጠረዥ 5)። ሠንጠረዥ 4፡ የማር ሙቀት መጠን ከማር ማጣበቅ ባህሪ ጋር ያለዉን ግንኙነትን የሚያሳይ ተ. ቁ የሙቀት መጠን (%) የማጣበቅ ባህሪ 1 13.7 600.00 2 20.6 189.60 3 29.0 68.4 4 39.4 21.4 5 48.1 10.7 6 71.1 2.6 ከሠንጠረዡ መረዳት የሚቻለው የማር የሙቀት መጠን ሲጨምር የማር መዝለግለግ ወይም ፈሳሽ የመሆን ሁኔታ ይጨምራል። እንዲሁም የማር የሙቀት መጠን ሲቀንስ የማር የመዝለግለግ ባህሪ ይቀንሳል። 2. እፍጋት እፍጋት ሌላው የማር አካላዊ ጠቃሚ ባህሪ ነው። የማር እፍጋት የሚገለፀው በእስፔስፊክ ግራቪቲ ሲሆን ይሄውም የማር እፍጋት ከውሃ እፍጋት ይበልጣል። የማር እፍጋት ሁኔታ በማር ውስጥ በሚገኘው የውሃ መጠን ይወሰናል። ይህ በማር ውስጥ የሚገኝ የውሃ መጠን መለያየት ማሩ በሚቀመጥበት ጊዜ ማሩ እና ውሃ በእፍጋት ልዩነት ተለያይቶ መቀመጥ በግልፅ የሚታይ ሲሆን በማር ውስጥ የሚገኘው የውሃ መጠን ሲጨምር የዉሃዉ እፍጋት ስለሚቀንስ ማሩ ላይ የተንሳፈፉ በማር ዉስጥ የሚገኝ ዉሃ እናገኛለን። ከማሩ ላይ ተንሳፎ የተቀመጠ ዉኃ ለረጅም ጊዜ ከቆየ ማሩ ወደ ቆምጣጣነት በመቀየር ማሩ እንዲበላሽ ያደርጋል። ይህ የማር መበላሸት እንዳይከሰት ማሩን በደንብ አድርጎ ማማሰል እና መቀላቀል አስፈላጊ ነዉ። የተለያዩ የዉኃ መጠን ያለዉ ማር እስፔሲፊክ ግራቪቲዉ ይለያያል። በማር ዉስጥ የሚገኘዉ የዉኃ መጠን ሲቀንስ 61 ስፔሲፊክ ግራቪቲዉ ይጨምራል እንዲሁም የማር የዉኃ መጠን ሲጨምር ስፔሲፊክ ግራቪቲዉ ይቀንሳል (ሰንጠረዥ 6)። የማር እፍጋት ባህሪን ማወቅ ለተመረተው የማር መጠን ምን ያህል የማር መያዣ በርሚል እንደሚያስፈልግ ለማወቅ ይጠቅማል። ለምሳሌ 21 ፐርሰንት ዉኃ ያለዉ ማር በአንድ ሊትር ውሃ የሚይዝ እቃ ቢቀመጥ እስከ 1.395 ኪሎ ግራም ማር መያዝ ይችላል። ሠንጠረዥ 5፡ የማር የወኃ መጠን መለያየት የሚፈጥረዉ የእስፔስፊክ ግራቪቲ ልዩነት የሚያሳይ የውኃ መጠን (%) ስፔስፊክ ግራቪቲ (%) ውኃ መጠን (%) ስፔስፊክ ግራቪቲ (%) 13.0 1.4457 18.0 1.4171 14.0 1.4407 19.0 1.4101 15.0 1.4350 20.0 1.4027 16.0 1.4295 21.0 1.3950 17.0 1.4237 3. እርጥበትንና ሽታን የመሳብ ባህሪ ማር በሚቆረጥበት፣ በሚጣራበት፣በሚቀመጥበት እንዲሁም በሚታሸግበት ወቅት ከአካባቢ እርጥበት እና ሽታን የመሳብ ባህሪ አለው። ማር ከአካባቢ እርጥበት እና ሽታን በመሳብ በማር ውስጥ የሚገኘውን የውሃ መጠን እንዲጨምር እና ጣዕሙ እንዲቀየር በማድረግ የማር ጥራት እንዲበላሽ ያደርጋል። የዉኃ መጠኑ 18.3% የሆነ ማር የአካባቢ አየር እርጥበት መጠን 60% በሆነ ቦታ ሲቀመጥ ከአካባቢው ርጥበት በመሳብ የውኃ መጠኑ እንዲጨምር ያደርገዋል። በመሆኑም ማር የምናስቀምጥበት እቃ ምንም አይነት ክፍተት የሌለው አየርም ሆነ ቅዝቃዜ የማያስገባና እና በደንብ የሚከደን መሆን አለበት። 4. የወለል ግትረት ማር እርጥበትን እና የተቀመጠበትን ቦታ ሳይለቅ እና ሳይበታተን የመቀመጥ ባህሪ አለዉ። ይህ ባህሪው ማርን ከሌሎች ነገሮች ጋር በመቀላቀል የኮስሞቲክ ምርቶችን ለማምረት እና በገበያ ተፈላጊ እንዲሆን በማድረግ በኩል ከፍተኛ ጥቅም እንዲሰጥ እና በገበያም ተፈላጊ እንዲሆን አድርጎታል። የማር ቦታ እና እርጥበትን ሳይለቅ የመቆየት ባህሪ ከመዝለግለግ ባህሪው ጋር ተዳምሮ ማር በሚሞቅበት ሰዓት አረፋ እንዲያወጣ ያደርገዋል። ይህ የማር ወለል ግትረት ባህሪ የማርን ጥራት ለመቆጣጠር ወይም ማር ከስኳር እና ሌሎች የተፈጥሮ ማር ያልሆኑ ነገሮች ጋር መቀላቀል እና አለመቀላቀሉን ለማወቅ ጠቃሚ ባህሪ ነው። በዚህ ዘዴ የማር አዳልትሬሽን ለመለየት ፈሳሹን ማር ከላይ ወደ ታች በምናፈስበት ወቅት ማሩ ሳይቆራረጥ የሚፈስ ከሆነ ማሩ አዳልትሬት አለመሆኑን ማወቅ ይቻላል። 62 ምስል 18. ፈሳሽ ማር ምንም ሳይቆራረጥ ሲፈስ እና ሳይበታተን ቦታ ሲይዝ የሚሳይ ምስል 5. የሙቀት ባህሪ ማርን በፀሐይ ብርሃንም ሆነ በሚፈላ ዉኃ በተገቢዉ ሁኔታ ለማሞቅ ማር ከሙቀት ጋር ያለዉን ባህሪ በሚገባ መረዳት ተገቢ ነዉ። እንዲሁም የማር ማቀነባበሪያ ለመትከል በሚታቀድበት ጊዜ የማር የሙቀት ባህሪያን በአግባቡ መረዳት ጥራቱን የጠበቀ ማር ለማቀነባበር እና ለገበያ ለማቅረብ ጠቃሚ ነው። የማር ሙቀት የመያዝ አቅም ከ0.56 እስከ 0.73 ካሎሪ/ግራም/በዲግሪ ሴንቲግሬድ ነው። ማር ሙቀት ለመያዝ የሚለያየበት ዋናው ምክንያት ማር በውስጡ የሚይዛቸው ንጥረ ነገሮች የተለያዩ መሆናቸዉ ሲሆን በተጨማሪም ማሩ ካለበት የጠጣርነት ደረጃ ጋር ይያያዛል።የማር ሙቀት የማስተላለፍ ባህሪዉ የተለያዬ ሲሆን መጠኑም ከ118 እስከ 143×10-~ካሎሪ/ሴንቲሜትር ስኩየር/ሰከንድ/በዲግሪ ሴንቲግሬድ ነዉ። እነዚህን ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን በኋላ የማር ሙቀት መጠን፣ ቅዝቃዜ መጠን እና መቀላቀል እንደ አስፈላጊነቱ በማካተት ማርን ማቀነባበር ተገቢ ነዉ። ማር ሙቀት የማስተላለፍ ባህሪው ዝቅተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በሙቀት ሊጎዳ ይችላል። በተለይ ማሩ መቅለጥ በጀመረበት የሙቀት መነሻ ቦታ ላይ ማሩ በሙቀት ሊጎዳ ስለሚችል ቶሎ ቶሎ ማማሰል ተገቢ ነዉ። ማርን ከትልቅ የማር ማቀነባበሪያ ማሽን ዉጭ በተለያዩ መንገዶች ማሞቅ የሚቻል ሲሆን በተለይ ማር የያዘዉን እቃ በሚፈላ ዉኃ ውስጥ በማድረግ ማሩን ማቅለጥ ጥራቱን የጠበቀ እና በሙቀት ያልተጎዳ ማር ማዘጋጀት ይቻላል። 63 6. ቀለም ፈሳሽ የሆነ የማር ቀለም ንፁህ ሆኖ የቀለሙ አይነት ከውኃ (ቀለም የሌለው) እስከ አምበር እና ጥቁር ቀለም ድረስ ይለያያል። ማር በተቀሰመበት እፅዋት፣ በቆየታ ጊዜ እንዲሁም በአቀማመጥ ምክንያት የተለየ ቀለም ሊይዝ ይችላል። ማር በዉስጡ ከሚይዛቸው ከማር ዉጭ ያሉ ሌሎች ነገሮች ለምሳሌ እንደ ድኝ (ፖለን) ከተቀላቀሉበት የማር ቀለም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ። ምስል 19፡ የተለያየ ቀለም ያለዉ ማር ማር ወደ ጠጣርነት ባህሪ ሲቀየር የማሩ ቀለም በአብዛኛው ነጣ ያለ ቀለም ይይዛል ይህም በውስጡ ከያዘው የጉልኮስ ቀለም የተነሳ የሚከሰት ነው። የማር ቀለም አስፈላጊነት በተጠቃሚው ህብረተሰብ የሚለካ ሲሆን በገበያ ዋጋ የተለያየ እንዲሆን ያደርገዋል። በመሆኑም እንደ ገበያ ተፈላጊነቱ የማር ቀለምን በሚመረትበት፣ በሚጣራበት እና በሚታሻግበት ወቅት በመለያያት እና በማዘጋጀት ወደ ገበያ ማቅረብ ተገቢ ነው። በአብዛኛው ጠቆር እና ቀላ ያለ ቀለም ያለው ማር ለኢንዱስትሪ አገልግሎትና ለጠጅ ሲውል ነጣ ያለ እና ቀላል ቀለም ያለው ማር በቀጥታ ለምግብነት አገልግሎት ይውላል። በቀጥታ ለምግብነት የሚቀርበዉ ማር የገበታ ማር ተብሎ ይጠራል። በአጠቃላይ የማር ቀለም ማርን ለገበያ በጅምላም ሆነ በችርቻሮ ለመሸጥ እንዲሁም ወደ ውጭ ለመላክ ወሳኝ የጥራት መለኪያ ነው። የማር ቀለም በፒፈንድ እስኬል ወይም መሳሪያ በሚሊ ሜትር የሚለካ ሲሆን ይህም ማርን በተለያዬ ቀለም አይነት ለመከፋፈል ይረዳል። የማር ቀለም በአሜሪካ የእርሻ ዲፓርትመን በፒፈንድ ስኬል ሲለካ ተለክቶ የሚሰጠዉን ዉጤት እንደሚከተለዉ ተዘርዝሯል (ሰንጠረዥ 7)። 64 ሠንጠረዥ 6: የማር ቀለም በፒ ፈንድ ስኬል ሲለካ የሚያሳይ ተ. ቁ የአሜሪካ የእርሻ ዲፓርትመንት የቀለም ስታንዳርድ (USDA) ፒፈንድ ልኬት Scale) (mm) የማር ቀለም 1 ውሃማ ቀለም (ነጣ ያለ) - Water white 0 to 8 2 ከፍተኛ የውሃማ ቀለም - Extra white > 8 to 17 3 ነጭ ቀለም - White > 17 to 34 4 ከፍተኛ ነጣ ያለ ቢጫ አምበር ቀለም - Extra light amber > 34 to 50 5 ነጣ ያለ ብሩህ ቢጫ አምበር ቀለም - light amber > 50 to 85 6 ብሩህ ቢጫ (አምበር) - Amber > 85 to 114 7 ጥቁር አምበር - Dark amber > 114 7. ጠጣርነት ከቀፎ ሲቆረጥ ፈሳሽ የነበረዉ ማር በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጠጣርነት ይቀየራል። የማር ጠጣርነትን ባህሪ በሚገባ ማወቅ አስፈላጊ ነው። ማር ጠጣር እንዲሆን የሚያደርገዉ ዋናው ምክንያት በማር ውስጥ የሚገኘዉ የስኳር መጠን ነው። ከማር ዉስጥ ከሚገኙ የስኳር አይነቶች ዉስጥ በተለይ ጉሉኮስ ማርን ጠጣር እንዲሆን በማድረግ በኩል ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነዉ። ጉሉኮስ ማርን ጠጣር እንዲሆን ከማድረጉም በተጨማሪ ጠጣር የሆነዉ ማር በቅርፅ ፣ በይዘት እና በጥራት የተለያዬ እንዲሆን ያደርገዋል። ከጉሉኮስ በተጨማሪም ማር ወደ ጠጣርነት እንዲቀየር የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶች በማር ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች ልዩነት እና የማሩ አቀማመጥ ናቸዉ። በማር ውስጥ ያለው የዉኃ መጠን አነስተኛ ከሆነ እና የጉሉኮስ መጠኑ ከፍተኛ ከሆነ ማር በሰዓታት ውስጥ ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት ይቀየራል። ማር ከዉስጣዊ ባህሪ በተጨማሪ በዉጫዊ ተፅዕኖ ወደ ጠጣርነት የሚቀየር ሲሆን በተለይ ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ ባለበት አካባቢ ከተቀመጠ በተወሰነ ጊዜያት ዉስጥ ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት ይቀየራል። ማርን ወደ ጠጣርነት እንዲቀየር ዉጫዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች የሚከተሉት ናቸዉ። • የአካባቢ የሙቀት መጠን ከ25 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ እና ከ5 ዲግሪ ሴንትግሬድ በታች በሆነ አካባቢ ማር ቢቀመጥ በአብዛሃኛው ፈሳሽ እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ሊቀመጥ ይቻላል። ነገር ግን የአካባቢ የሙቀት መጠን በአማካኝ 14 ዲግሪ ሴንትግሬድ ከሆነ ማር በፍጥነት ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት ይቀየራል። • በተጨማሪም በማር ውስጥ ሌሎች ከማር ውጭ የሆኑ ባዕድም ሆኑ ጠቃሚ ሌሎች ነገሮች ለምሳሌ ድኝ (ፖለን) ከተቀላቀሉበት ከፈሳሽ ወደ ጠጣርነት ይቀየራል። • እንዲሁም ማር በሙቀት በሚቀልጥበት ወቅት በደንብ ካልተማሰለ እና ካልተዋሃደ ማር ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት ቶሎ ይቀየራል። በአብዛሃኛው ማር ቀስ እያለ ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት የሚቀየር ከሆነ በጣም ጠንካራ ጠጣርነት ከመፍጠሩም በተጨማሪ የተለያየ ማራኪ ያልሆነ ቅርፅ እንዲይዝ ያደርገዋል። ይህም በገበያ ላይ ተፈላጊነቱን ይቀንሰዋል። 65 በመሆኑም ማር የለሰለሰ ይዘት እንዲኖረዉ ጠጣር መሆን በጀመረበት ጊዜ በደንብ በማማሰል በገበያ ተፈላጊ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ምስል 20፡ የተለያዩ ነገሮች የተቀላቀሉበትና ወደ ጠጣርነት የተቀየረ ማር አንዳንድ ማር ከፈሳሽ ወደ ጠጣርነት ሲቀየር ከማር ውስጥ የሚገኘው ውኃ ከላይ በኩል ተንሳፎ ይቀመጣል ይህ ሁኔታ ደግሞ ማር ወደ ኮምጣጤነት እንዲቀይር በማድረግ ማሩ እንዲበላሽ ያደርገዋል። በመሆኑም በዚህ መልክ ወደ ጠጣርነት የተቀየረን ማር ቶሎ ቶሎ በደንብ በማማሰል ማሩ ከዉኃ ጋር እንዲዋሀድ በማድረግ ችግሩ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል። ምስል 21፡ ውኃው ተለይቶ የተንሳፈፈ በአጠቃላይ ማር ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት በተፈጥሮ የመቀየር ባህሪ ያለዉ ሲሆን ነገር ግን ይህ ባህሪው በአንዳንድ ተጠቃሚዎች የተሳሳተ ግንዛቤ በማሳደሩ የተነሳ ወደ ጠጣርነት የተቀየረ ማር ከሌሎች እንደ ስኳርና ሌሎች ነገሮች ጋር ተቀላቅሏል (አዳልትሬት) ብለው እንዲያምኑ አድርጓል። ማር የሚሰጣቸው ጥቅሞች ማር ከጥንት ጀምሮ ለሰው ልጅ ምግብነት በተለይም የስኳር ፍላጎትን ለማርካትና ለኃይል ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ከምግብነት በተጨማሪም ለተለያዩ በሽታዎች በመድኃኒትነት ሲያገለግል ቆይቷል፣ አሁንም በጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። የማር የመድኃኒትነት ጥቅም በሳይንቲስቶች የተረጋገጠ ሲሆን ማር በአጠቃላይ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይሰጣል። 1. በንጥረ ነገር የመለጸገ ምግብ፡ ማር ለሠውነት ጥንካሬ ከመስጠቱም በተጨማሪ ከፍተኛ ድካም ለማስወገድም ይጠቅማል። የማር ጥቅም ብዙ ሲሆን በኃይል ሰጭነቱ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነዉ። 2. ማር ምግብ እንዲፈጭ እና ከሰዉነታችን ጋር እንዲዋሃድ ከማድረጉም በተጨማሪ ደም 66 ለፈሰሰዉ ሰዉ ደምን ቶሎ ለመተካት እና ኃይል ለማግኘት ጠዋሚ ነዉ። ማር በአሁኑ ወቅት ለምግብነት፤ለምግብ ማዋሀጃ፤ከተለያዩ ነገሮች ጋር በመቀላቀል የተለያዩ በሽታዎችን ለማዳን በመድኃኒትነት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ምስል 22፡ ማር በዳቦ፣ በብስኩትና ሌሎች ምግቦች ጋር ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ሲዉል ማር ማምረት እና ማቀነባበር የንብ ውጤቶችን በሚፈለገዉ መጠን ለማምረት የንብ መንጋ (ሰራተኛ ንቦች) ቁጥር ወሳኝ ሲሆን የንብ መንጋዉ ቁጥር ከፍተኛ መሆን በተወሰኑ ቀናት እፅዋቶች አብበዉ ወደ ፍሬ ሳይቀየሩ ከአበባዉ የሚያገኙትን የአበባ ፈሳሽ ክፍል እና ዱቄት በወቅቱ በመሰብሰብ ወደ ማር እና ወደ ድኝ በመቀየር በከፍተኛ መጠን እንዲመረቱ ያደርጋሉ። በአገራችን ማር የሚመረትባቸው ሁለት ዋና ዋና ወቅቶች አሉ። አንደኛው እና ዋነኛው ከጥቅምት አጋማሽ እስከ ታህሳስ አጋማሽ ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ከሚያዚያ አጋማሽ እስከ ግንቦት መጨረሻ ያለው ነው። በተለያዩ አካባቢዎች በተለምዶ ማር መድረሱ የሚታወቅባቸዉ መንገዶች የሚከተሉት ናቸው፡- • ቀፎ ያለበት አካባቢ ማር ማር ይሸታል • ማታ ማታ ብዙ ንቦች በቀፎው አንቀጽ (አይነ-ብልጥ) ላይ ሰፍረው ይታያሉ • በአይነብልጡ አካባቢ የሞቱ ድንጉላ ንቦች ይታያሉ • ቀፎው ሲከፈት የማር እንቆራው በማር ተሞልቶና በአዲስ ነጭ ሰም በስሱ ተሸፍኖ ይታያል። እነዚህ ምልክቶች ሲታዩ ማሩ ሳይቆይ መቆረጥ አለበት። የማር ምርት መብሰሉን ካረጋገጥን በኋላ ንቦች ሳይመገቡት የማር ምርቱን በወቅቱ መሰብሰብ አለበት። ማር በሚቆረጥበት ጊዜ ለንቦች የሚሆን ማር በበቂ ሁኔታ መቀመጥ አለበት። ማርን ለንቦች በበቂ ሁኔታ በማስቀረት ንቦች ለሚቀጥለው ዓመት ጠንካራ ሆነው እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል። ለንቦች በቂ ማር ለመተዉ ማር በሚቆረጥበት ጊዜ በሚከተለዉ ሁኔታ የምናገኘዉን ማር ለንቦች መተዉ እንችላለን፡- 67 • አብዛኛው የእንጀራ ክፍሉ ያልተሸፈነ ከሆነ፣ • የተወሰነ የእንጀራ ክፍል በማር እና በድኝ ከተሸፈነ፣ • እንዲሁም እንጀራዉ የተወሰነ ክፍሉ እጭ እና የተወሰነ ክፍሉ ማር ከሆነ። ማርን ከባህላዊ እና ከርብራብ ቀፎ በምንቆርጥበት ጊዜ የማር እንጀራውን በየቀለሙ መለየት ተገቢ ነው። በዚህ መልክ ማርን በየቀለሙ በመለየት በመቁረጥ እና በማጣራት ጥራቱን የጠበቀ ማር ለገበያ ለማቅረብ ይቻላል። በመሆኑም በጥቁር፣ በቢጫ እንዲሁም በነጭ እንጀራ ላይ የተሰራን ማር በተለያዩ እቃዎች በመቁረጥ እና በማስቀመጥ እና ከተጣራም በኋላ በየቀለሙ ለገበያ እንዲቀርብ ማድረግ በገበያ ተፈላጊ እንዲሆን ከማድረግም በተጨማሪ የተሻለ ዋጋ ማግኘት ይቻላል። ማር ከቀፎ ከተቆረጠ በኃላ በተለይ በባህላዊ እና ርብራብ ቀፎ የተመረተውን ማር እንጀራው ሳይሰባበር እና ሳይፈተፈት ለገበያ ቢቀርብ የተሻለ ዋጋ ያስገኛል። ማር በሚቆረጥበት ሰዓት ሽታ አልባ ጭስ መጠቀም ይኖርብናል። ነገር ግን ጠንካራ ጠረን ያለው ጭስ እና ጭሱንም በብዛት የምንጠቀም ከሆነ በማሩ ጥራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ የማሩም ጣዕም እንዲበላሽ ያደርጋል። ምስል 23፡ ከፍተኛ ጭስ በመጠቀም ማር ሲቆረጥ ማር በሚቆረጥበት፣ በሚሰበሰብበት፣ በሚጣራበት እና በሚታሸግበት ጊዜ የማር ጥራቱን የማያበላሹ እቃዎችን በመለየት መጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ማር ለገበያ ለማቅረብ እና የተሻለ ዋጋ ለማስገኘት ያስችላል። የማር ጥራት ሲባል ሶስት ዋናዋና ነገሮችን ይይዛል 1. የተፈጥሮ ቀለሙ 2. የተፈጥሮ ጣዕሙ እና 3. በውስጡ የሚይዛቸው ንጥረ ነገሮች (ውኃ፣ ጉሉኮስ፣ ፍሩክቶስ እና የመሳሰሉትን) ያጠቃልላል። 68 ምስል 24. እንጀራ ማር ከርብራብ ቀፎ ሲቆረጥ ለማር መያዣነት የምንጠቀምባቸው እቃዎች በደረጃዎች እና ጥራት ተቆጣጣሪ ድርጅት የተረጋገጡ መሆን አለባቸዉ። ማር በውስጡ ከፍተኛ አሲድ ስላለው እንደ ኮፐር፣ ብረት፣ ዚንክ በመሳሰሉት ማዕድናት በተሰሩ እቃዎች መቀመጥም ሆነ መነካካት የለበትም። ነገር ግን ለምግብ መያዣ ተብሎ የተዘጋጀ ፕላስቲክ፣ የማይዝግ ብረት እና አልሙኒየም በተሰራ እቃ ማስቀመጥ እንዲሁም በብርጭቆ እና ጃምጃር ጎማ አሽጎ ማቅረብ ማር ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ እንዲቀመጥ ያደርገዋል። ምስል 25፡ የተለያዩ የማር መያዣ ዕቃዎች በሃገራችን የተለያዩ የማር መያዣ ዕቃዎች ጥቅም ላይ ውልዋል። እነዚህም ዕቃዎች በማር ጥራተ ላይ አሉታዊ ትፅዕኖ ይሚያሳድሩ እንደ ሽክላ ማስሮ፣ የእንስሳት ቆዳ (ስልቻ)፣ ቅል፣ ለሌላ አገልግሎት የውሉ ዕቃዎች የመሳሰሉት የገኙበታል። የማር ዕቃነ በተመለከተ የማር ጠራቱን ጠብቆ ለማቆየት ለማከማቸት እና ለማከፋፈል የሚያስችሉ፣ የተለያዩ አማራጮች አሉ። አንዳንድ ታዋቂ ምርጫዎች እንመልከት። 1. የጠርሙስ ማር መያዣዎች; የጠርሙስ ማሰሮዎች ውብና ለእይታ ማራኪ ናቸው። እነሱ በተለያዩ ቅርጾች እና መጠኖች ይዘጋጃሉ ፣ የመስታወት ማሰሮዎች የማርን ተፈጥሯዊ ቀለም እና ይዘት ለማሳየት ጥሩ ናቸው። በተጨማሪም እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ እና ለማጽዳት ቀላል ናቸው። 69 2. የፕላስቲክ የማር መያዣዎች;- o የፕላስቲክ የማር መያዣዎች ቀላል ክብደት ያላቸው፣ ረጅም ጊዜ የሚቆዩ እና ለመሰባበር ያልተጋለጡ ናቸው። o የፕላስቲክ የማር መያዣዎች ለዕለታዊ አጠቃቀም ምቹ ናቸው እና ብዙ ጊዜ ለጅምላ ማሸጊያዎች ያገለግላሉ። 3. ልዩ የማር ማሰሮዎች፡- የሴራሚክ የማር ማሰሮ፣ ከእንጨት የተዘጋጁ ያጌጡ ማሰሮዎች፣ ክሪስታል የማር ማሰሮ፣ ሚኒ ጃርስ የመሳለሉት ይገኙበታል። ልብ ይበሉ፡- አንዳንድ የማር መያዣዎች ማርን በቀላሉ ወደሌላ ዕቃ ለመገልበጥ ወይም ለማፍሰስ አብሮ የተሰሩ ማፋሰሻ ቧምቧዎች ይኖራቸዋል። ማርዎን ትኩስ እና ጣፋጭ ሆኖ ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ከምግብ ደረጃ የተዘጋጁ ቁሶች የተሰሩ የማር መያዣዎችን መምረጥ እና ትክክለኛ አየር፣ እርጥበትና ሽታ የማያስገባ ክዳን ያላቸው መሆናቸውን ያረጋግጡ! ማር ማጣራት ማር ማጣራት ማሩን ከሰም እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች በተለያዩ የማጣሪያ ዘዴዎች መለየት ማለት ነው። ማርን በምናጣራበት ወቅት ማሩ ከተቆረጠ በኋላ በማሩ ውስጥ የሚኖረው የሙቀት መጠን የማሩን ፈሳሽነት እና የማጣበቅ ባህሪውን ስለሚቀንሰው ማር ከተቆረጠ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ማጣራት ሂደት ማስገባት ጥራቱን የጠበቀ ማር ለማምረት ይረዳል። ከፍሬም ቀፎ የተሰበሰበ ማር የምናጣራበት ዘዴ በፍሬም ቀፎ ማር ማጣራት ማለት በተወጠረ የፍሬም ሽቦ የተያዘዉን የእንጀራ ማር ከቀፎ ውስጥ ከተሰበሰበ በኋላ በእንጀራዉ ውስጥ የተቀመጠዉን ማር ሙሉ ለሙሉ ከእንጀራዉ በማስወጣት የማጣራት ዘዴ ነው። ከፍሬም ቀፎ የተመረተውን ማር ለማጣራት የሚከተሉት እቃዎች ያስፈልጋሉ።  የአይነበጎ መግለጫ ሹካ  ባለ ሦስት እና ከዚያ በላይ ፍሬም ሽቦ የሚይዝ ማር ማጣሪያ  የማር መያዣ ክዳን ያለው ባልዲ  የተጣራዉን ማር ለመግፈፊያ የሚያገለግል ማንኪያ  ከፍሬም ቀፎ የተሰበሰበውን የፍሬም እንጀራ በመጀመሪያ ማጣሪያው ከማስገባታችን በፊት በአይነበጎ መግለጫ ሹካውን በመጠቀም የተሸፈነውን አይነበጎ በጥንቃቄ መግለጥ፣ በመቀጠል በማር ማጣሪያ ውስጥ ማስገባት እና ማጣሪያውን በማሽከርከር ከእያንዳንዱ አይነበጎ ቀዳዳ ውስጥ ያለው ማር ተሟጦ እስኪያልቅ ድረስ ፍሬሙን እያገላበጡ ማሩን ማጣራት። 70  ማሩን በማጣሪያው ከተጣራ በኋላ ከማሩ ጋር የተቀላቀሉ የሰም ሰፈፍ እና ሌሎች ነገሮችን መለየት ያስፈልጋል። ከተጣራዉ ማር ጋር የተቀላቀሉትን ሰፈፍ እና ሌሎች ነገሮች በሁለት መንገድ መለየት እንችላለን። እነሱም፡- 1. የተጣራውን ማር በደንብ ካማሰሉ በኋላ ማቆየት የተጣራዉ ማር ከማር ማጣሪያ ከወጣ በኋላ እና በማር መቀበያ እቃ ውስጥ ከተጠራቀመ በኃላ ከማሩ ጋር ተቀላቅለው የገቡትን ሌሎች ነገሮች በክብደታቸው ተንሳፈው እንዲለዩ ለማድረግ ማሩን በደንብ ማማሰል እና እስከ 12 ሰዓት ማቆየት። በዚህ ሰዓት ከማሩ ጋር የተቀላቀሉት ሠፈፍም ሆነ ሌሎች ባዕድ ነገሮች ወደ ላይ በመንሳፈፍ ይቀመጣሉ። በመጨረሻም ባዕድ ነገሮችን በማንኪያ ከላይ በማንሳት ንፁህ እና የተጣራ ማር በዚህ ዘዴ ማግኘት ይቻላል። 2. ወንፊት በመጠቀም የተጣራዉን ማር መለየት ከማር ማጣሪያዉ ተጣርቶ የወጣን ማር የበለጠ ለማጣራት እና ማሩ በማጣሪያ በሚጣራበት ጊዜ ተቀላቅለዉ የገቡ ሰፈፍ እና ሌሎች ነገሮችን ለማጣራት በማር መለያ ወንፊት (ድርብ ወንፊት) ወይም ጨርቅ (ናይለን ጨርቅ/አቡጀዲ) በመጠቀም ማሩን ማጣራት ይቻላል። ምስል 26፡ ከፍሬም ቀፎ የተመረተ ማር፣ የተሸፈነ ማር በማር መግፈፊያ ቢላዋ ሲገፈፍ፣ በማር ማጣሪያ ሲጣራ እና በድርብ ወንፊት ማሩ ከማጣሪያ ወጥቶ ሲጣራ ከባህላዊ እና ርብራብ ቀፎ የሚገኝን ማር ማጣራት ከባህላዊ እና ርብራብ ቀፎ የሚመረቱትን የማር እንጀራ ሳይሰባበሩ እና ጉዳት ሳይደርስባቸዉ በመቁረጥ ጥራቱን ጠብቆ በማጣራት ለገበያ ማቅረብ ይቻላል። ከባህላዊ እና ከርብራብ ቀፎ የሚገኘዉን ማር ለመቁረጥ እና ለማጣራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች፡-  ቢላዋ  መከደን የሚችል ሠፊ ጉድጓዳ ሣህን  ማር መጭመቂያ  ማር መቀበያ ባልዲ እና ሌሎቹም ከባህላዊ እና ርብራብ ቀፎ የሚቆረጠዉ ማር እንጀራ ማሩ አብዛኛው ክፍሉ የአይነበጎ ቀዳዳ የተሸፈነ መሆን አለበት። በዚህ መልኩ የተቆረጠ ማር የዉሃ መጠኑ በገበያ ተፈላጊ እንዲሆን ከማድረጉም በተጨማሪ ማሩ ሳይበላሽ እንዲቆይ ያደርገዋል። በዚህ መልኩ የተቆረጠዉን ማር 71 በየቀለሙ በመለየት ለማጣራት ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በየቀለሙ የተለየዉን ማር ከቀፎ ከተቆረጠ በኋላ ወዲያውኑ የሙቀት መጠኑ ሳይቀንስ ማጣራት ያስፈልጋል። ማሩን ለማጣራት የሚከተሉትን አሰራሮች በመከተል ማሩን በጥራት ማጣራት ይቻላል። እንጀራውን በደንብ አድርጎ መፈትፈት የተፈተፈተዉን ማር ከ6-12 ሰዓት ማቆየት እና ሰፈፉ እና ባዕድ ነገሮች ወደ ላይ እንዲሳፈፉ ማድረግ። ከዚያም ከላይ የተንሳፈፉ ነገሮችን በማንኪያ ማንሳት እና መለየት። በመጨረሻም ያልተለየ ባዕድ ነገር ካለ የተጣራውን ማር በድርብ ወንፊት ወይም ጨርቅ (ናይለን ወይም አቡጀዲ) አድርጎ ማጣራት። በጨርቅ ያደረግነዉ ማር በመጭመቂያ ማሽን ውስጥ በማስገባት መጭመቅ እና ማጣራት ይቻላል። ምስል 27፡ ድርብ ወንፊት በመጠቀም ማርን ማጣራት ጠጣር ማርን የምናጣራበት ዘዴ ከቀፎ የተሰበሰበው ማር በተለያዩ ምክንያቶች ሳይጣራ ለብዙ ጊዜ ከተቀመጠ እና ማሩ ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት ከተቀየረ የሚከተሉትን ቅደም ተከተሎች በመከተል ማሩን ማጣራት ይቻላል። በመጀመሪያ ጠጣሩን ማር ከጠንካራ ጠጣርነት ወደ ለስላሳ ይዘት እስኪቀየር በደንብ ማማሰል ያስፈልጋል። በመቀጠል ውኃ በትልቅ ማሞቂያ እቃ ውስጥ እንዲፈላ በማድረግ ማር የያዘውን እቃ ከሚፈላው ውኃ ውስጥ በማስገባት ማሩን ማሞቅና እንዲቀልጥ ማድረግ ይቻላል። ማሩ መቅለጥ ሲጀምር ሁሉም የማር ክፍል ተመሳሰይ ሙቀት እንዲያገኝ እየሞቀ እና እየቀለጠ ያለውን ማር ማማሰል ያስፈልጋል። በመጨረሻ ማሩ ከጠጣርነት ሙሉ ለሙሉ ወደ ፈሳሽነት ሲቀየር ማር ማሞቁን እና ማቅለጡን ማቆምና ወደ ማጣሪያ ማስተላለፈ ይገባል። 72 ምስል 28፡ ጠጣር የሆነን ማር በሚፈላ ዉሃ ለማቅለጥ የምንጠቀምባቸዉ እቃዎች በዚህ መልክ የቀለጠዉን ማር ከ6 እስከ 12 ሰዓት ማቆየት እና ሰፈፉ እና ባዕድ ነገሮች ወደ ላይ እንዲንሳፈፉ ማድረግ ይቻላል። ከዚያም የተንሳፈፈውን ሰፈፍ እና ሌሎች ነገሮች በማንኪያ ማንሳት ወይም መግፈፍ። ከዚያም ማሩን ጨርቅ ወይም ድርብ ወንፊት በመጠቀም ማጣራት ይቻላል። ጠጣር ማርን በፈላ ውኃ በማሽን በምናሞቅበት እና በምናቀልጥበት ሰዓት የውሃ መጠኑ 17.5 በመቶ የሆነን ማር በሚከተለው የሙቀት መጠን እና ቆይታ እያማሰልን ማሞቅ ተገቢ ነው (ሰንጠረዥ 9)። ሠንጠረዥ 7: ጠጣር ማርን በተለያየ የሙቀት መጠን እና የቆይታ ሰዓት የሚቀልጥበት ሁኔታ ተ. ቁ ጠጣር የማር መጠን በኪግ በ40 0C የሙቀት መጠን በ45 0C ሙቀት መጠን በ50 0C የሙቀት መጠን 1. 20 ኪ.ግ 24 ሰዓት 18 ሰዓት 16 ሰዓት 2. 50 ኪ.ግ 48 ሰዓት 36 ሰዓት 24 ሰዓት 3. 80 ኪ.ግ 108 ሰዓት 72 ሰዓት 60 ሰዓት 4. 300 ኪ.ግ - 108 ሰዓት 72 ሰዓት ይህ የሙቀት መጠን እና ቆይታ በኤሌክትሪክ ለሚሰራ ማሽን የሚያገለግል መረጃ ሲሆን ነገር ግን የሙቀት ምንጫችን በእንጨት (እሳት) የሚያመጣ ሙቀት ከሆነ ቶሎ ቶሎ ጠጣሩን ማር በማማሰል ማሩ ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት ሙሉ ለሙሉ ሲቀየር ማር ማቅለጡን በማቆም ወደ ቀጣይ የማጣራት ሂደት መግባት ይቻላል። ማርን በመጋዘን ማከማቸት ማር እንዲቀመጥ በተገለፁት የማር መያዣ እቃዎች ማለትም በጠርሙስ፣ስቴንለስ እስቲል (የማይዝግ ብረት)፣ ለምግብ መያዣነት ተብሎ በተሠራ ፕላስቲክ ጎማ መያዝ እና መቀመጥ 73 አለበት። ማር ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ እንዲቀመጥ አየር እና ቅዝቃዜ በማያስገባ በደንብ በተከደነ እቃ መያዝ ይኖርበታል። በዚህ መልኩ የተያዘ ማር በደረቅ፣ ፀሃይ እንዲሁም እርጥበት እና ቅዝቃዜ በማያገኘው የማከማቻ መጋዘን ከተቀመጠ ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት የጣዕምም ሆነ የቀለም ለውጥ ሳያመጣ እና ሳይበላሽ መቀመጥ ይችላል። ማር ከተቀመጠበት እቃ ወደ ሌላ እቃ መገልበጥ ካስፈለገ የሚገለበጥበት እቃ በደንብ ታጥቦ፣ ከደረቀ በኋላ ምንም ዓይነት ጥሩም ሆነ ሌላ ሽታ የሌለው መሆኑን ከተረጋገጠ በኋላ ማሩን ማስቀመጥ ያስፈልጋል። የማር ማከማቻ መጋዘን የቤቱ ውስጥ ሙቀት መጠን ወደ 20ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የተጠጋ ቢሆን እና የአካባቢ የእርጥበት መጠንም 65 ፐርሰንት ቢሆን ተመራጭ ነው። ነገር ግን የመጋዘን የሙቀት መጠን ከ25 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ከሆነ በማር ጥራቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ማርን በመጋዘን በምናስቀምጥበት ጊዜ ሌላው ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ጠቃሚ ነገር ማሩ ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት ከተቀየረ በኋላ ጠጣር የሆነው ማር በውስጡ የሚገኘውን ውኃ ወደ ላይ እንዲንሳፈፍ ስለሚያደርገዉ እና ማሩ ወደ ጠጅነት (ፈርመንቴሽን) ስለሚቀየር እና ስለሚበላሽ ማሩን በየጊዜው በማማሰል በደንብ እንዲቀላቀል በማድረግ ችግሩ እንዳይከሰት መከላከል ይቻላል። የማር ጥራትን የምንቆጣጠርባቸው መንገዶች የማር ጥራት ማለት ማሩ ከቀፎ ከተመረተ በኋላ የተፈጥሮ ቀለሙን፣ የተፈጥሮ ጣዕም እና ቃናውን እንደያዘ ለተጠቃሚው እንዲደርስ ማድረግ ነው። በተጨማሪም የማርን ጥራት የምንቆጣጠረው ማሩ በንቦች የተሠራ የተፈጥሮ ማር መሆኑን ለማረጋገጥ እና ቀጥሎም ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር ያልተቀላቀለ መሆኑን ለማወቅ እንዲረዳ ነው። በመጨረሻም ጥራቱን የጠበቀ ማር በሚፈለገው ደረጃ ተቀነባብሮ ለገበያ እንዲቀርብ ስለሚረዳ ነው። በአገራችን የተፈጥሮ ማርን ከስኳር እና ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር በማቀላቀል ከእውነተኛው ጋር እኩል በሚመስል መልኩ ለገበያ ስለሚቀርቡ አብዛኛው የማር ተጠቃሚ ህብረተሰብ ትክክለኛውን ማር ከተቀላቀለው ማር ለመለየት አስቸጋሪ አድርጎበታል። የተፈጥሮ ማርን ከሌሎች እንደ ስኳር ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር መቀላቀሉን ለመለየት በተለያዩ መንገዶች ማወቅ ይቻላል። 1ኛ. በላብራቶሪ፡ በማር ውስጥ የሚገኙትን ንጥረ ነገሮች በላብራቶሪ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ውጤቱ የሱክሮስ መጠኑ ከ8 ፐርሰንት በላይ ከሆነ ማሩ ከስኳር ጋር የተቀላቀለ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። 2ኛ. በፊዚካል (አካላዊ) የማር ለዉጥ፡ ማሩን በመቅመስ እንዲሁም የመዝለግለግ ሁኔታውን በማየት ከስኳር እና ሌሎች ነገሮች ጋር መቀላቀሉን መለየት ይቻላል። በመዝለግለግ ባህሪዉ የተፈጥሮ ማርን ለመለየት ፈሳሽ የሆነ ማርን ወደ ታች በምናፈስበት ጊዜ ማሩ ከሚፈስበት እቃ አንስቶ ታች እሰከ ሚያርፍበት ድረስ ሳይቆራረጥ 74 እንዲሁም ከመቀበያ እቃዉ ሲቀመጥ ካልተበታተነ የተፈጥሮ ማር መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል። ነገር ግን ማሩ ሲፈስ የሚቆራረጥ ባህሪ ካለው የተፈጥሮ ማር ሳይሆን ማሩ ከሌሎች ነገሮች ጋር የተቀላቀለ መሆኑን ማወቅ እና መለየት ይቻላል። በተጨማሪ ማሩም በጣም ቀጭን እና የውሃ መጠኑ ከፍተኛ ይሆናል። 3ኛ. በማሟሟት፡ ሌላው የተቀላቀለ (አዳልትሬት) ማርን የምንለይበት ዘዴ